በኮንስትራክሽን ዘርፉ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመረጃ ቋት አለመኖሩ ስራ ተቋራጮች እንዳሻቸው ስራዎችን እንዲይዙ እያደረገ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የህንጻ ስራዎች ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ በረከት ተዘራ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት፣ ክልሎችን ከባለስልጣኑ ጋር በጋራ የሚያስተሳስር የመረጃ ቋት አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡
ይህም አንዱ ክልል ላይ ስራዉን በአግባቡ ያላከናወነ ስራ ተቋራጭ ሌላ ክልል ሄዶ እንዳሻዉ የሚሰራበት ክፍተት የሚፈጥር አሰራር ሆኗል ብለዋል፡፡
ጥሩና ደካማ አፈጻጸም ያሳዩ ተቋራጮችንም መለየት አልተቻለም ነዉ ያሉት ሀገር አቀፍ የመረጃ ቋት ቢኖር ግን መረጃዉን በቀላሉ ማግኘት ስለሚቻል ማን ምን አቅምና ጠንካራ አፈጻጸም እንዳለዉ በቀላሉ መለየት ይቻል ነበር ነዉ ያሉት፡፡
በየክልሉ ያሉ የግንባታ ፍቃድ የወሰዱ ስራ ተቋራጮችንና አማካሪዎችን የማናውቅበት ሁኔታ ተፈጥሯልም ብለዋል አቶ በረከት፡፡
በዚህም የአፈጻጸም ችግር ያለባቸው ስራ ተቋራጮች የሚይዟቸው ግንባታዎች መጓተት ይገጥማቸዋል፤ ከዚህ በተጨማሪም የግንባታ ሂደቱ ጥራቱን የጠበቀ አይሆንም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የፕሮጀክት ምዝገባ ባለስልጣኑ የራሱን ዳታ ቤዝ አዘጋጅቶ እየሰራ መሆኑንም አቶ በረከት ነግረዉናል፡፡
በመቅደላዊት ደረጀ
መጋቢት 06 ቀን 2013 ዓ.ም











