ቻይና በጨረቃ ደቡባዊ ዋልታ ላይ በጨረቃ ላይ ጥናትና ምርምር የሚካሄድበት ጣቢያን ለማቋቋም እቅድ እንዳላት የሀገሪቷ የህዋ ሳይንስ ምርምር ጣቢያ አስታውቋል፡፡
ጣቢያው እንደገለጸው፣ በጨረቃ ገጽ ላይ ለመገንባት የታቀደውን ማእከል እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ቅድመ ጥናቶች ተጠናቀዋል ብሏል፡፡
ቻይና ከአንድ ወር በፊት ወደ ጨረቃ ሰው አልባ መንኮራኩር በማስወንጨፍ ከጨረቃ ላይ ለናሙና የሚያገለግሉ አለቶችን ማምጣቷ ይታወሳል፡፡
አለቶቹ በጨረቃ ዙሪያ ከሚደረጉት ጥናቶች በተጨማሪ አሁን ለሚገነባው የምርምር ማእከል ጥናት ተደርጎባቸዋልም ተብሏል፡፡
የቻይና የህዋ ሳይንስ ምርምር ጣቢያ ሃላፊው ው ዌረን፣ የአሁኑ እቅድ በጨረቃ ላይ የሚደረግ 4ተኛ ፕሮግራም ሲሆን እቅዱን ለማሳካት ወደ ጨረቃ 3 የሳተላይት ጉዞዎች ይደረጋሉ ብለዋል፡፡
እነዚህም ቻንግ 6፤ 7 እና 8 የተባሉ ሳተላይቶች እንደሆኑ አመላክተዋል፡፡
ሃላፊው ማዕከሉን ለምን በጨረቃ ደቡባዊ ዋልታ ላይ ለመገንባት ተመረጠ ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ፤ የጨረቃ የዙሪትና የሽክርክሪት ጊዜ እኩል 28 ቀናት በመሆኑ ይህም በዚሁ የጨረቃ ክፍል ተከታታይ የሆኑ 180 ብርሃናማ ቀናት በመኖራቸው ነው ብለዋል፡፡
እነዚህ ቀናቶች ምንም አይነት ጨለማ የማይታዩባቸው በመሆናቸው ጥናቱን ለማካሄድ የሚጠቅሙ በመሆናቸው ናቸው ብለዋል፡፡
ሃላፊው እቅዱን እውን ለማድረግ ሀገራቸው ቻይና ከሩሲያ የጠፈር ምርምር ማእከል ልምድ እንደምትወስድ አስታውቀዋል፡፡
ሙሉ ግንባታው እ.ኤ.አ ከ2021-2025 ባሉት አመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሲ ጂ ቲ ኤን
በጅብሪል ሙሃመድ
መጋቢት 06 ቀን 2013 ዓ.ም











