በተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች የዜጎች በህይወት የመኖር መብት አደጋ ላይ መዉደቁን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ መምጣቸው አሳስቦኛል ብሏል፡፡

ኢሰመጉ አሰፈላጊው ሕጋዊ እርምጃ ተወስዶ የዜጎች ደህንነት መጠበቅ እንዳለበት ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላቶች ሲያሳስብ መቆየቱንመ ገልጿል፡፡

ሆኖም አሁንም የዜጎች የሰብዓዊ መብቶች እየተጣሱ ደህንነታቸውም ከዕለት ወደ ዕለት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን አረጋግጫለሁ ነዉ ያለዉ፡፡

በኦሮምያ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን በ27/06/2013 ዓ.ም በቤተክርስቲያን ውስጥ ምዕመናንና ካህናትን ጨምሮ 29 የሚደርሱ ንጹሃን ዜጎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የገለጸዉ ኢሰመጉ፣ከነዚህም ውስጥ የ22 ሰዎች የቀብር ስነ-ስርዓታቸው ሲፈጸም የቀሪዎቹ አስክሬን ደግሞ በፍለጋ ላይ እንደሚገኝ የመረጃ ምንጮቼ አረጋግጠዉልኛል ነዉ ያለዉ፡፡

አሁን እየወጡ ያሉ መረጃዎች የሟቾች እና የተጎጂዎች ቁጥር በእጥፍ ሊያሻቅብ እንደሚችል የሚያመላክቱ መሆናቸዉንም አስታዉቋል፡፡

በሌላ በኩል በደቡብ ብሔር ብሔርሰቦች እና ሕዝቦች ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ ከኦሮምያ ክልል ጋር በምስራቅ ጉጂ ዞን በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ከወሰን ማስከበር እና በተለያዩ አስተዳደራዊ ጥያቄዎች መነሻነት ግጭቶች እየተፈጠሩ ለሰው ሕይወት መጥፋት ፤ ለአካል ጉዳት እና ለንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑን ቀጥሏል ነዉ ያለዉ ኢሰመጉ፡፡

ይህንንም ችግር ለመፍታት ከሁለቱም ወገኖች በተመረጡ የሀገር ሽማግሌዎች ፤ የሀይማኖት መሪዎች እንዲሁም የወረዳ አመራሮች ለዉይይት በተሰባሰቡበት በ29/06/2013 ዓ.ም በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ከአማሮ ልዩ ወረዳ 6 ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች 6 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው አስታዉሷል፡፡

እነዚህ ድርጊቶች የሚያመላክቱትም ኢትዮጵያ ተቀብላ ያጸደቀቻቸዉ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች ማቆሚያ የሌለው ጥሰቶች እየተፈጸሙ መሆኑንና መንግስትም እነዚህን መብቶች ለማክበር አስፈላጊ ሁኔታዎችን የማሟላት ግዴታውን በሚጠበቀው መጠን እየተወጣ እንዳልሆነ እንዳልሆነ መሆኑን ኢሰመጎ ጠቁሟል፡፡

አሁንም መንግስት የዜጎቹን ሰብዓዊ መብቶች እና ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነቱን በአግባቡ የማይወጣ ከሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ወደከፋ ደረጃ መድረሱ አይቀሬ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ሲል አሳስቧል፡፡

መንግስት ገለልተኛ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት በአካባቢዎቹ ተንቀሳቅሰው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታዎችን ለማጣራት የሚያስችላቸውን ሁኔታ እንዲያመቻች በድጋሚ ኢሰመጉ አሳስቧል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
መጋቢት 08 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.