የአማራ ክልል መንግስት የወሰደብኝን ከ 6 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ሊመልስልኝ ይገባል ሲል ህብር ስኳር አክሲዮን ማህበር ጠየቀ፡፡

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ለስኳር ልማት የወሰደውን 6 ሺህ 183 ሄክታር የኢንቨስትመንት መሬት እንዲመለስለት ሕብር ስኳር አክሲዮን ማህበር ጠይቋል።

ማህበሩ እንዳለዉ በክልሉ አዊ ዞን ጃዊ ወረዳ እና ምዕራብ ጎጃም ዞን ደቡብ አቸፈር ወረዳ ወስዶት የነበረውን የኢንቨስትመንት መሬት የክልሉ መንግስት ገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቢሮ ነጥቆታል፡፡

መሬቱን የተነጠቀበት አግባብ ተገቢ ባለመሆኑ መሬቱ ሊመለስልኝ ይገባል ሲል ጠይቋል፡፡

ሕብር ስኳር አክሲዮን ማህበር በስኳር ልማት ዘርፍ ለመሰማራት በ2004 ዓ/ም ከአማራ ብሄራዊ ክልል መንግስት 6 ሺህ 183 ሄክታር መሬት ወስዶ እንቅስቃሴ ቢጀምርም፣ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች እንቅፋት ፈጥረውበት የኢንቨስትመንት ፈቃዴን ተነጥቄ ከባለአክሲዮኖች የሰበሰብኩትን ብር እንደያዝኩ እስካሁን ወደ ስራ መግባት አልቻልኩም ብሏል።

ማህበሩ በ2007 ዓ/ም ከብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ ጋር መሬቱን ከማዘጋጀት ጀምሮ ፋብሪካ ተክሎ እስከማስረከብ ድረስ ስራውን አጠናቆ እንዲያስረክበዉ ከ165 ሚሊዮን ዶላር በላይ ስምምነት ፈርሞ እንደነበር ገልጿል፡፡

ይሁን እንጂ ሜቴክ አክስዮን ማህበሩ የሰጠውን ውል ወደ ጎን በመተውና የመሬት ዝግጅቱን ሳይጀምር በመቅረቱ መሬቱ እንዲነጠቅ ምክንያት መሆኑንም ማህበሩ አስታዉቋል፡፡

ማህበሩ አሁን ይህን መሬት የክልሉ መንግስት ሊመልስልኝ ይገባል ሲል ጠይቋል፡፡

በረድኤት ገበየሁ
መጋቢት 10 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *