በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የጽኑ ህሙማን ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ የኦክስጅን እጥረት ማጋጠሙ ተነግሯል።
በአስተዳደሩ 4 የመተንፈሻ መሳሪያ(mechanical ventilator) ያሉ ቢሆንም በሚገባ አገልግሎት እየሰጡ ያሉት 2ቱ ብቻ ናቸው ተብሏል።
በአሁኑ ሰአትም በድሬዳዋ ከተማ 7 ሰዎች ኦክስጅን እየተጠቀሙ እንዳሉ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የኮቪድ ህክምና አስተባባሪ ትግስቱ የማነ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።
የኦክስጅን እጥረቱ ያጋጠመው ጮራ የተሰኘው የኦክስጅን አቅራቢ ኩባንያ ተቃጥሏል በመባሉ ነው ብለዋል አስተባባሪው።
በድሬዳዋ ከተማ ኦክስጅን የሚያቀርብ ፋብሪካ ባለመኖሩም በጣም ተቸግረናል ሲሉ አክለዋል።
ከዚህ በኋላ ሁለትና ሶስት ሰአት ብቻ የሚያቆይልን ኦክስጅን ነው ያሉት ።
ክትባትን በተመለከተ እስካሁን በከተማዋ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪዎች ክትባት መውሰዳቸው የተነገረ ሲሆን ከሰኞ ጀምሮ ግን ለሁሉም ለማዳረስ ይሰራል ተብሏል።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭቱ በእጅጉ እየጨመረ በመሆኑ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው ሀላፊው ጠቁመዋል ።
በመቅደላዊት ደረጀ
መጋቢት 11 ቀን 2013 ዓ.ም











