ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ውጭ በህዳሴው ግድብ ላይ ሌላ አደራዳሪ እንደማትፈልግ በድጋሜ አስታወቀች፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ ከአፍሪካ ህብረት ውጭ ሌላ አደራዳሪ አያስፈልግም ነው ያለው።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ በመስጠት ላይ ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ አዲስ አደራዳሪ እንዲገባ አትፈቅድም ብለዋል።

ግብፅና ሱዳን በድርድሩ ላይ አሜሪካ ፣የአውሮፓ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ጣልቃ እንዲገቡ ግፊት እያደረጉ ቢሆንም በኢትዮጵያ በኩል ግን ተቀባይነት እንደሌለው ነው የተገለፀው።

የህዳሴው ግድብ ድርድር መካሄድ ያለበትና ልዩነቶች መፈታት ያለባቸው በአፍሪካውያን እንደሆነ ኢትዮጵያ ታምናለች ያሉት አምባሳደር ዲና ይህም ለአፍሪካ ባለን ክብር ነው ብለዋል።

በሱዳን በኩል እንደመከራከሪያ ሀሳብ የሚነሳው የግድቡን የግንባታ ጥራት እና ደህንነት በሚመለከትም ቃል አቀባዩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ደህንነቱና ጥራቱ ያልተጠበቀ ግድብ ፈፅሞ አልገነባችም ይህንን ደግሞ ሱዳኖችም ያውቁታል መንግስትም በተደጋጋሚ ስለግድቡ ለሱዳን መንግስት ገለፃ ሰጥቷል ነው ያሉት አምባሳደር ዲና።

የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድሩ በአራት አደራዳሪዎች ማለትም፣ በአሜሪካ ፣በአውሮፓ ህብረት፣ በአፍሪካ ህብረትና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይካሄድ የሚለውን ግን ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው ቃል አቀባዩ አስምረውበታል።

ይሁን እንጅ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ጋር ለመወያየት ዝግጁ ስለመሆኗም ተሰምቷል ።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
በአባቱ መረቀ
መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *