የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ትናንት የምርጫ ማኒፌስቶውን (የቃል ኪዳን ሰነዱን) ይፋ አድርጓል።
በተለያዩ ዘርፎች ላሉ የሀገራችን ችግሮች የመፍትሄ አማራጮችን ይዟል ተብሏል ሰነዱ።
ለሀገራችን ዘረፈ ብዙ ችግሮች ዋና መንስኤ ከ30 አመታት በላይ ስራ ላይ የዋለው የብሄር ፖለቲካ ነው ብሏል ፓርቲው።
አክራሪነትና ብሔርተኝነት ወቅታዊው የሀገራችን ነባራዊ የፖለቲካ ማጠንጠኛ ሆኖ ሳለ ፤ የችግሮቻችን መነሻ የብሔር ፖለቲካ ነው ሲል የሚነሳ ማኒፌስቶ በመላ ሀገሪቱ ተቀባይነት ያገኝ ይሆን? የኢትዮ ኤፍ ኤም ጥያቄ ነው:-
የብሄር ፖለቲካ ይሄን ያህል አመት በሀገሪቱ ስራ ላይ ሲውል በርካታ ተከታዮችን አላፈራም ወይ? በሀገራችን የሚስተዋለው ግጭትና መፈናቀልስ የሚነግረን እሱን አይደለም ወይ? የኔ አካባቢ ነው ውጣልኝ በሚል የሚፈጠር ትርምስ የሚያሳየው በሀገራችን የአክራሪና የፅንፈኛን መበርከት አይደለም ወይ? በዚህ ሁኔታ የናንተ ማኒፌስቶ ( የቃል ኪዳን ሰነድ) በመላ ሀገሪቱ ገዢ አግኝቶ ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ አያደርገውም ወይ ሲል ጣቢያችን ላቀረበው ጥያቄ የኢዜማው መሪ ፕሮፌሰር ብርሀኑ በርግጥ ከ 30 አመታት በላይ በሀገሪቱ የነገሰው የብሄር ፖለቲካ ሀገራችን ለገባችበት ዘርፈ ብዙ ችግር ምክንያት ነው ብለን እናምናለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የብሄር አመለካከት ገዢ እንዳገኘ ተደርጎ የሚነገረው ልክ አይደለም ያሉት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ባለፈው ሰላሳ አመት ተግባራዊ ስለተደረገ ብቻ እንዲህ ያለ ድምዳሜ ላይ ልንደርስ አይገባም፣ አለበለዚያ ኮምዩኒዝምም በአስራ ሰባት አመቱ የደርግ ስርአት ተቀባይነት አግኝቷል ፤ ልንል ነው ፤ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አንድ እምነት፣ አንድ አመለካከት፣ አንድ አደረጃጀት ፤ በህብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው የሚለካው እንዴት ነው ሲሉ የሚጠይቁት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ብቸኛው መለኪያው ምርጫ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
በአሁን ሰአት በኢትዮጵያ ውስጥ የትኛው ነው ገዢ ሀሳብ የሚለው የሚታወቅበት ሌላ ዘዴ ስለሌለ ሁሉም ያለምንም ፍርሀት በነፃነት የሚቀበለውን አመለካከት መምረጥ አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በኛ እምነት የብሔር ፖለቲካ በተለይ ሰርቶ በሰላም መኖር በሚፈልገው ሰላማዊ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ተቀባይነት አለው ብለን አናምንም ያሉ ሲሆን ምርጫው ፍትሀዊ እንዳይሆን ሊደርሱ የሚችሉ ማናቸውንም ፈተናዎች እስከመጨረሻው በጋራ ልንታገላቸው ነው የሚገባው ብለዋል ፕሮፌሰር ብርሀኑ
ፕሮፌሰር ብርሀኑ ብሄርን መሰረት ባደረገ ፖለቲካ የመጣ ችግርን በብሔር በመደራጀት ለመፍታት መሞከር በበሽታው መንስኤ ህመሙን ለማከም መሞከር ነው ሲሉ ይሄ መንገድ መጨረሻው እልቂት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ብቸኛው መፍትሄው የሚገኘው ይላሉ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ብቸኛው መፍትሄ የሚገኘው በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ከምናገኘው ዜግነታችን ነው ብለዋል፡፡
በሄኖክ አስራት
መጋቢት 15 ቀን 2013 ዓ.ም











