ለኩላሊት ንቅለ ተከላ የሰጪና ተቀባይ የተስማሚነት ምርመራ በኢትዮጵያ ሊጀመር ነዉ ተባለ፡፡

አርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀዉ ለኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና የኩላሊት ሰጪና ተቀባይ የተስማሚነት ምርመራ በአገር ዉስጥ በቅርቡ ይጀመራል ብሏል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የቲቢና የዉስጥ ደዌ ክፍል ሃላፊና የተስማሚነት ላቡራቶሪ አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ቅድስት መኮሻ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ፤ ወደ ዉጭ አገር ይላክ የነበረዉ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የሰጪና ተቀባይ ተስማሚነት ምርመራ በአገር ዉስጥ ለመጀመር እየተሰራ ነዉ ብለዋል፡፡

የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና በቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል እንደሚሰጥ የሚታወቅ ቢሆንም የኩላሊት ሰጪና ተቀባይ ተስማሚ ስለመሆናቸዉ ለማረጋገጥ ወደ ዉጪ ይላካሉ፡፡

በቅርቡ ግን በአርማዉር ሀንስን የምርምር ኢንስቲትዩት አማከኝነት በአገረ ዉስጥ አገልግሎቱ እንደሚጀምር ዶክተር ቅድስት ነግረዉናል፡፡

የአገልግሎቱ መጀመር የህሙማንን እንግልት ከመቀነሱ በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የዉጭ ምንዛሬን ጥረትን እንደሚያስቀርም ተገልጧል፡፡

ዘርፉ ብቁ የሰዉ ሃይል ስለሚፈልግ ባለሙያዎች የተለያ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ እየተሰራ እንደሆነና ፤ የህከምና መሳሪያዎችም እየተሟሉ እንደሚገኙ ታዉቋል፡፡

ለዚህም መንገስት አስፈላጊዉን ትብብር እና ድጋፍ እንዲያደርግ ዶክተር ቅድስት ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምናን ለመስጠጥ የሰጪና ተቀባይ የደም ናሙና ወደ ህንድ ፤ ጀርመን እና ዱባይ የመሳሰሉ አገራት በመላክ ምርመራ ከስደረገች በኋላ በቅዱስ ጳዉሎስ ሆስፒታል ሕክምናዉ እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡

በአባቱ መረቀ
መጋቢት 20 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.