እውን በታሪካችን ለመጀመርያ ጊዜ በመረጥነው መንግስት እንተዳደር ይሆን?

አንድ ቀን ወደ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በተቃረብን ቁጥር ወደ አዕምሯችን ይበልጥ እየቀረበ የሚመጣ ጥያቄ አለ፡፡

ይህ ጥያቄ ስጋት ያዘለ ጥያቄ ነው፤ ይህ ስጋት ያዘለ ጥያቄ ዝም ብሎ አልተፈጠረም ፤ የኋላ ታሪካችን የወለደው የጭንቅ ጥያቄ ነው፡፡

እውነት ድምፃችን ይከበርልን ይሆን? በታሪካችን ለመጀመርያ ጊዜ በመረጥነው መንግስት እንተዳደር ይሆን?

የዚህ ጥያቄ በጎ መልስ በገዢው ፓርቲ፣ ምርጫ ቦርድን በመሰሉ በገለልተኛ ተቋማት፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ በመራጩ ህዝብ ድምር ቀናነትና ቆራጥነት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ይታመናል፡፡

ደግሞ ይሄው ጥያቄ ሌላ የጭንቅ ጥያቄን ይወልዳል፡፡

እውን አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ በታሪካችን ለመጀመርያ ጊዜ በመረጥነው መንግስት እንደምንተዳደር የሚያረጋግጥልን ነው?

ለዛሬ ኢትዮ ኤፍ ኤም ይሄን ጥያቄ ይዞ ዋና ተዋናዮቹን ፓርቲዎችን አናግሯል፡፡

ከገዢው ፓርቲ ብልፅግና እንጀምር ፤ መጫወቻ ሜዳውን ገና ካሁኑ እያጠበባችሁ ነው በሚል እየተከሰሳችሁ ነው፤ ይሄ ክስ ምን ያህል እውነትነት አለው?
የብልፅግና ፓርቲ አቶ ዛድግ አብርሀ በዲሞክራሲ ልምምድ ላይ የምንገኝ፤ታዳጊ ሀገርና ታዳጊ ዲሞክራሲ ያለን በመሆናችን እኛም ጋር ሌሎችም ጋር ችግሮች ይኖራሉ ብለዋል፡፡

መዋቅራዊ ችግሩን ተባብረን መፍታት አለብን የሚሉት አቶ ዛድግ፣ ከፓርቲዎች የሚመጡልንን አቤቱታዎች በቅንነት ከመፍታት ጎን ለጎን የውሸትና የበሬ ወለደ ክሶችን እናጋልጣለን ብለዋል፡፡

ሆኖም ግን የፖለቲካ ምህዳሩ በጣም ሰፍቷል ያሉ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ምርጫዎች ሁሉ የተሻለ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አይ እሱስ ብዙ መብቶች እያፈኑ ምህዳሩ ሰፍቷል ማለት ቀልድ ነው የሚለው ደግሞ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ነው፡፡

በሂደቱ በመሳተፍ ነው ለውጥ ማምጣት የምንችለው ብለን ነው እንጂ ፤ የምርጫ ተወዳዳሪዎቻችን በመታሰራቸው ክስ ላይ እኮ ነን የሚሉት የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ ጌታነህ ባልቻ ናቸው፡፡

የ አዲስ አበባን የአስተዳደር ጥያቄ መልስ ለመስጠት በእያንዳንዷ ነገር ህዝቡ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በበኩሉ ምርጫ ቦርድ ነው ተስፋችን ይላል፡፡

የብቃት ማነስ ቢኖርም ፣ ቦርዱ ገለልተኛ ነው ብለን እናምናለን ፣ እስካሁንም ያን አረጋግጦልናል ብሏል፡፡

በመንግስት በኩልስ?
በኢዜማ ብሄራዊ ምርጫ ዘመቻ ኮሚቴ ውስጥ የዋና ዋና ሚዲያዎች አስተባባሪ ትዕግስት ወርቅነህ ፤ በመንግስት በኩል ቃል የተገቡልን ነገሮች እየተፈፀሙ አይደለም ይላሉ፡፡

አባላቶች ብቻ አይደሉም ከተመዘገቡ ጊዜ ጀምሮ እጅ ከፍንጅ ካልተያዙ በወንጀል የማይጠየቁ ተመራጮች እየታሰሩብን ነው ያሉ ሲሆን፣ ፎቶ ለምን አነሳችሁ፣ ለኢዜማ መወዳደራችሁን የማታቆሙ ከሆነ ከስራችሁ ትፈናቀላላችሁ ፤በሌሊት ቤቱ ተንኳኩቶ ከምርጫው እንዲወጣ ዛቻና ማስፈራሪ ማድረስ እና ሌሎችም ብዙ ፈተናዎች እያጋጠሙ ነው፤ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሶ ለመቀስቀስ ለፓርቲዎች ችግር ይሆናል፣ ተብሎ የሚሰጋው፤ አክራሪና ፅንፈኛ ብሄርተኛ ነው፡፡

በእያንዳንዱ የኢትጵያ ጥግ እየተንቀሳቀስን ነው ፤ በዚህ እንቅስቃሴያችን ያረጋገጥነው ፤ በ ሀገራችን ሰላምን፣ አብሮ መኖርን ፣ አንድነትን እና ኢትዮጵያን የሚወድ በጣም እንደሚበዛ ነው ብለዋል ትዕግስት ወርቅነህ ፡፡

ለእነዚህ ኢትዮጵያውያን ቃል የምንገባላቸው ወደ ኋላ አንልም የሚለውን ነው ሲሉ ተናግረዋል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፤ በበኩሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳው እየጠበበ ነው የመጣው ይላል፡፡
የአብን የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ጣሂር መሀመድ ፤ ፓርላማው ውስጥ ቅቡልነት ያላቸው ፓርቲዎች ተወክለዋል ለመባል ነው ግስጋሴያችን ሁላ የሚመስለው ብለዋል፡፡

እንደ ምርጫ ቦርድ ያሉ ገለልተኛ ተቋማት ብዙ የሚመሰገን ጎን እንዳላቸው ሁሉ ሊደፈኑ የሚገባቸው በርካታ ክፍተቶች አሏቸው የሚሉት አቶ ጣሂር፣ የፀጥታ ተቋማት፣ ፍርድ ቤት፣ የሰብአዊ መብት ተቋማት፣ ገዢው ፓርቲ ታሪካዊ ሀላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው ነዉ ያሉት፡፡

ለደጋፊዎቻቸውና ለአማራ ህዝብ ስሜት የሚፈታተኑ፤ አስቸጋሪ ወቅቶችን እያለፍን ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ ሌላ ሀገር የለንምና ሀገራችንን የሚጎዳ ምንም ነገር ማድረግ የለብንም፣ ስነ ምግባራችንን ጠብቀን በምርጫ ካርዳችን መብታችንን እናስከብር ሲሉ የአደራ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ፓርቲያችን ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ለማገዝ በርካታ ነገሮችን ሰርቷል የሚሉት ከብልፅግና ፓርቲ አቶ ዛድግ አብርሀ፤ ሁሉም ሀገራችን የተረጋጋና የዳበረ ዲሞክራሲ ባለቤት እንድትሆን የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስታልፈዋል፡፡

በሔኖክ አስራት
መጋቢት 22 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.