በሁሉም ቦታ በደርሰው ጥቃት የአጸፋ እርምጃ በክልልና በፈዴራል መንግሥት ቅንጅት እየተወሰደ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ በኦሮሚያ ክልል በምእራብ ወለጋ ዞን በንጹሐን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በፌስቡክ ገጻቸዉ ላይ እንዳሉት፣ የተሰማንን ጥልቅ ኀዘን ለሟች ቤተሰቦችና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ እንገልጻለን፡፡

ዓለማችን በወረርሽኝ ተጨንቃ መፍትሔ በምትፈልግበት በዚህ ሰዓት፣ ሆን ብለው በሰዎች ላይ መከራና ስቃይ የሚጨምሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች በምንፈልጋት ኢትዮጵያ ውስጥ ስፍራ የላቸውም ብለዋል።

ጠላቶቻችን በውስጥና በውጭ ተደራጅተው ንጽሐን ዜጎቻችንን በመግደል የጀመርነውን ጉዞ ለማሸማቀቅና ከመንገዳችን ለማስወጣት ጥረት እያደረጉ ነው።

መሥዋዕትነት እየከፈልንም ቢሆን የኢትዮጵያን አንድነት አጠናክረን ጉዟችንን እንቀጥላለን።

በሁሉም ቦታ በደርሰው ጥቃት አጸፋ እርምጃ በክልልና በፈዴራል መንግሥት ቅንጅት እየተወሰደ ይገኛል ነዉ ያሉት።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ ጥፋት ኃይሎች ወጥመድ ላለመውደቅ በማስተዋል እየተጓዘ፤ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ከመንግሥት ጋር ተባብሮ ጥፋተኞችን ወደ ሕግ ለማቅረብ እና እንደዚህ ዓይነት ግድያዎች ፈጽመው እንዲቆሙ በትብብር ልንሠራ ይገባል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።

ኢትዮጵያ በመሥዋዕትነት የቆመች፤ በመሥዋዕትነት የምትቀጥል ሀገር ናት ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ በትብብርና በአንድነት መንፈስ የኢትዮጵያን ጠላቶች ደግመው እንዳይነሡ አድርገን ማጥፋት አለብን ብለዋል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.