በፍቅረኛው ላይ አሰቃቂ የግድያ ወንጀል ፈፅሞ አስክሬኗን ቆራርጦ የጣለው ወንጀለኛ በዕድሜ ልክ እስራት ተቀጣ፡፡

የ26 ዓመቷ ወጣት ራሄል በሲቪል ኢንጅነሪንግ የትምህርት መስክ ተመርቃ በስራ ላይ የምትገኝ ወጣት ነበረች፡፡ ከተከሳሹ ከድር ሽፈራው ጋር የፍቅር ጓደኝነት እንደነበራቸው እና ከቤተሰቦቿ ጋርም እንደተዋወቀ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በምርመራ ወቅት አረጋግጧል፡፡

መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ/ም ተከሳሽ ከድር ሽፈራው ፍቅረኛው ተከራይታ የምትኖርበት ቤት ሄዶ ተያይዘው እንደወጡ እና ከዚያ በኋላ ወደቤት እንዳልተመለሰች ቤተሰቦቿም መስከረም 27 ቀን 2011 ዓ/ም ወደ ፖሊስ ቀርበው እንዳመለከቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡

መስከረም 26 ቀን 2011 ዓ/ም ከቀኑ 5 ሰዓት ገደማ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ወረዳ 9 አዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጀርባ የተቆራረጠ የሰው አካል በሁለት ፌስታል ተጠቅልሎ መንገድ ላይ ተጥሎ ተገኝቷል የሚል መረጃ እንደደረሰው እና አስክሬኑም የሴት እንደሆነ በማረጋገጥ ምርመራ ማጣራት መጀመሩን የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስክሬኑ ተጥሎ ከተገኘበት ስፍራ ባሰባሰበው የቴክኒክ ማስረጃ መነሻነት ከድር ሽፈራውን በ 1 ወር ውስጥ በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራውን መቀጠሉን አስታውቋል፡፡ በተያዘበት ወቅትም የፍቅረኛው የወጣት ራሄል ሞባይል ስልክ እጁ ላይ እንደተገኘ እና የወርቅ የአንገት ሃብሏንም አድርጎት እንደነበር ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

ከድር ሽፈራው ወንጀሉን አልፈፀምኩም ብሎ ለመካድ ቢሞክርም የኋላ ኋላ ፖሊስ ባደረገው ጥልቅ ምርመራ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ገርጂ ወፍጮ ቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ መስከረም 26 ቀን 2011 ዓ/ም ከለሊቱ 10 ሰዓት ገደማ የግድያ ወንጀሉን ፈፅሞባት አስክሬኗን ቆራርጦ በፌስታል ካደረገ በኋላ እንዳይታይ በሻንጣ ውስጥ በመክተት ታክሲ ተኮናትሮ ወስዶ እንደጣለው በማመን ቃሉን ሰጥቷል፡፡

ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ተከሳሽ ከድር ሽፈራው በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ያስተላለፈበት መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡-ምክትል ኢንስፔክተር እመቤት ሀብታሙ

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *