ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ በቅድሚ ሰላሟን ማስጠበቅ እንዳለባት ተነገረ፡፡

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ እነሆ 10 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

የታላቁ የኢትዮጲያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ አማካኝነት ልክ የዛሬ 10 ዓመት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ/ም የፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠለት፡፡

እነሆ ይህ እቅድ ተይዞ ወደ ስራው ከተገባም 10 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡

ግድቡ ስራው ሲጀመር በአምስት አመታት ውስጥ ሊጠናቀቅ ቢታለምም ይህ ሊሆን ግን ፈፅሞ አልቻለም፡፡

ለምን ካሉ ምክንያቱ ብዙ ነው ይሉናል የውሃ ዲፕሎማሲ ኤክስፐርቱ አቶ አበበ ይርጋ፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን አስመልክቶ ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸው ቆይታ ባለሙያው እንደነገሩን፣ ግድቡ በተያዘለት ጊዜ እንዳይጠናቀቅ ካደረጉ ዋና ዋና ምክንያቶች ውስጥ በዋናነት በሃገራችን እየተከሰተ ያለው የፀጥታ መደፍረስ አንዱና ዋናዉ ችግር ነው ብለዋል፡፡

ምንም እንኳን ለህዳሴው ግድቡ ግንባታ መዘግየት ሌላኛው ችግር ከልክ ያለፈው ሙስኝነት እንደሆነ ያነሱልን ባለሙያዉ፣ ያለው ከሌለው የህብረተሰብ ክፍል በሙሉ ኪሱን አራግፎ ጠብ ያደረጋት የላቡ ፍሬ በሙሰኞች መበዝበዙ ግድቡ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ፍሬ እንዳያፈራ አድርጎታልም ብለውናል፡፡

በርግጥ ግብፅ በየጊዜው አሉታዊ የሽረባ መረቧን መዘርጋቷ ከጅምሩ እስካሁኑ ድረስ የቀጠለችበት ፀባይዋ ቢሆንም ነገር ግን ይሄ የግብፅ ሴራ እኛ ጋር ካለው ችግር በላይ አይደለም ትርጉምም የለውም ብውናል ባለሙያው፡፡

ሃገራችን ከገባችበት የፖለቲካ ውጥንቅጥ በተለይም በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች ላይ እየታየ ያለው የፀጥታ መደፍረስና ለህዳሴው ግድቡ በግብፅና በ ሱዳን በኩል ያለው እስጣ ገባ እንዲሁም ሌሎችም ችግሮች በርግጥም ዛሬም አስር ዓመታትን ለተሻገረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እራስ ምታት ሆነውበት ቢቀጥሉም፣ በሃገሪቱ ያለው የፀጥታ ሁኔታ መረጋጋት እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አይነተኛ መፍትሄ መሆኑን ነው አቶ አበበ በአጽንኦት የተናገሩት፡፡

በየዉልሰዉ ገዝሙ
መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *