የዘረ መል ምርምር መጀመሩን የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

ኢንስቲትዩቱ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀዉ፤ የዘረ መል ምርምር እና ጥናቶች በተለያዩ የበሽታ አይነቶች ላይ ምርምር ማድረግ ጀምሪያለሁ ብሏል፡፡

ከተመሰረተ ከ50 ዓመት በላይ ያስቆጠረዉ ይህ የምርምር ተቋም፣ አሁን ላይ በአፍሪካ የመጀመሪያዉን የዘረ መል ምርመራ እና ጥናት መጀመሩን የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አለምሰገድ አብዲሳ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በኮቪድ 19 ዙሪያም የሚደረገዉ የምርምር ሂደት ተጠናክሮ ቀጥሏል ነዉ ያሉት፡፡

የዘረ መል ምርምር በኢትዮጵያ መጀመሩ፤ የተለያዩ የቫይረስ አይነቶችን ምንነትና ባህሪ ለመረዳት ስለሚያግዝ የአገሪቱን የህክምና ዘርፍ እንደሚያሳድግም ተነግሯል፡፡

በኢትዮጵያ አስተባባሪነትም የዘረ መል ምርምሩ በኤርትራ፤ በሱዳን እና በካሜሮን አገራት እንደሚደረግም ታዉቋል፡፡

በህክምናዉ ዘርፍ ከሚደረገዉ የዘረ መል ጥናቶች በተጨማሪም በተለያዩ መስኮች ላይ የዘረ መል ምርምር ለማድረግ የሚያስችል መሳሪያ አገር ዉስጥ እንደገባም ታዉቋል፡፡

በምርምር ማዕከሉ በቫይረስ የሚመጡ በሽታዎች የምርምር ማዕከል መሪ የሆኑት ዶክተር አንዳርጋቸዉ ሙሉ በበኩላቸዉ፣ የዘረ መል ምርምር የቫይረሶችን ምንነት እና ባህሪ ለማወቅ ይረዳል ነዉ ያሉት፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ይሄዉ ዘረ መል ምርምር የኮሮና ቫይረስን አዲስ ዝርያ ባህሪ እንዲሁም የክትባቶችንና የመድሃኒቶች ተስማሚነት ለማወቅ ጥናቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለዉም ዶክተር አንዳርጋቸዉ ተናግረዋል፡፡

የህክምና ጠቢባን የሰዉን ልጅ ከተለያዩ ህመሞች ለመታደግ ሲሉ ሌት ተቀን የተለያዩ የምርምር ስራዎችን ያከናዉናሉ፡፡

በተለይም በዚህ ዘመን የህመም አይነቶችና ወረርሽኞች ባህሪያቸዉን እየለዋወጡ ያሉበት በመሆኑ፤ አገራት ከፍተኛ በጀት መድበዉ ለእነዚህ የህመም አይነቶች ፈዋሽ መድሃኒቶችንና ክትባቶችን እያመረቱ ይገኛሉ፡፡

ይሁን እንጂ የምርምር ስራዉን በዋናነት የበለፀጉ አገራት ቢከናዉኑም፤ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ገና በማደግ ላይ ያሉ አገራት በራሳቸዉ አቅም በዘርፉ ያን ያህል ርቀት እየተጓዙ አይደለም፡፡

እናም የበሽታዎች ባህሪ በአስቸጋሪ ሁኔታ እየተለዋወጠ እንደመጣ ባለሙያዎች የሚያስረዱ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ለህክምናዉ ዘርፍ ትኩረት በመስጠት የምርምር ማዕከላትን ማስፋፋት ይጠበቅባታል ተብሏል፡፡

በአባቱ መረቀ
መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *