በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አውታር ላይ ዝርፊያ የፈጸሙ ሦስት ግለሰቦች እጅ ከፍንጅ ተያዙ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀዉ፣
በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ቡልቡላ ወረዳ 12 አካባቢ መጋቢት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡00 ገደማ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አውታር ላይ ዝርፊያ ሲፈፅሙ የነበሩ ሦስት ግለሰቦች ከአካባቢው ነዋሪዎች በተሠጠ ጥቆማ በህግ አካላት እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል ተብሏል፡፡

በዝርፊያው 2 ሺህ 250 ሜትር የመካከለኛ መስመር ማስተላለፊ መስመሮች፣ 42 የምሰሶ ስኒዎች እና አራት የእንጨት ምሶሶዎች ከጥቅም ውጭ መሆናቸዉንም የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ አገልግሎት አስታዉቋል፡፡
በዚህ ምክንያትም በኮዬ ፈጬ ያሉ ደንበኞችና በአካባቢው የሚገኙ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ታዎሮች የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንደተቋረጠባቸዉም ሰምተናል፡፡

ግለሰቦቹም በቦሌ ቡልቡላ ፖሊስ ጣቢያ በሚገኙ የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኙና በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አውታሩ ላይ በደረሰው የስርቆት ወንጀል ተቋሙ ከ353 ሺህ 623 ብር በላይ ኪሳራ ደርሶበታል ተብሏል፡፡
በአሁን ወቅትም በተዘረፈው የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት አውታር ምክንያት የተቋረጠውን አገልግሎት ወደነበረበት ለመመለስ የምስራቅ አዲስ አበባ ዲስትሪክት የኦፕሬሽን ሜይንቴናንስ ክፍል በቦታው ተገኝቶ የመልሶ ጥገና ስራ እያከናወነ ይገኛል ተብሏል፡፡

የቴሌኮሚኒኬሽን እና የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት አውታሮችን ለመጠበቅ ሲባል በወጣው አዋጅ ቁጥር 464/97 መሰረት የክልል እና የከተማ መስተዳደሮች እንዲሁም የኤሌክትሪክ ዘርፍ ተጠሪ ተቋማት በቴሌኮሚኒኬሽን እና በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶችን ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችና ስርቆቶችን የመከላከልና የመጠበቅ ሃላፊነት እንዳለባቸዉ ተቋሙ አሳስቧል፡፡

ህብረተሰቡም መሰረተ ልማቱ የህዝብ ሃብት እንደመሆኑ መጠን፣ እንደራሱ ንብረት በንቃት በመጠበቅ ከመሰል እኩይ ተግባር እንዲከላከል እንዲሁም በመሠረተ ልማቱ ላይ ጥገና እናደርጋለን በማለት የሚነካኩ ግለሰቦች ሲመለከት በተቋሙ የተመደቡ ሠራተኞች መሆናቸውን የሚገልፅ መታወቂያ መያዛቸውን ማረጋገጥ ይገባዋል ተብሏል፡፡

ከዚህ ባሻገር የሚያጠራጥር ሁኔታ ሲከሰት ለፀጥታ አካላት ማሳወቅ እንደሚገባ እንዲሁም ወደ በ905 ነፃ የጥሪ ማዕከል መደወል ወይም በአቅራቢያ ለሚገኝ የተቋሙ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ጥቆማ ማድረግ እንደሚገባም የኢትጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አሳስቧል፡፡

በአባቱ መረቀ
መጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.