ኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን የሚያግዝ መርሃ ግብር ይፋ አደረጉ፡፡

አገራቱ የመጀመረያ ደረጃ ተማሪዎች ጥሩ ክህሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መርሃ ግብር በዛሬው እለት ይፋ አድርገዋል።

መርሃ ግብሩን በይፋ የከፈቱት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስያ ፓሲፊክ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሞላልኝ አስፋውና በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አልቡስራ ባስኑር ናቸው።

የኢንዶኔዥያ ኤምባሲ ባዘጋጀው በዚህ መርሃ ግብር ላይም የሁለቱ አገራት ህፃናት ተማሪዎች የልምድ ልውውጥ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ የ60 ዓመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዳላቸው የገለፁት አምባሳደር አልቡስራ ባስኑር በቀጣይም አገራቸው ከኢትዮጵያ ጎን ትሆናለች ነው ያሉት።

በተለይም የሁለቱን አገራት ህፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን በማቀራረብ የዕውቀት፣ የቴክኖሎጂና የባህል ልውውጥ እንዲኖራቸው ያስችላል ብለዋል ።

ይህ መርሃ ግብር በሁለት አገራት መካከል ሲካሄድ በአፍሪካ ብቻም ሳይሆን በአለም የመጀመሪያው መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ፣ ኢንዶኔዥያ ለኢትዮጵያ ወጣቶችና ህፃናት ድጋፍ ማድረጓን ትቀጥላለች ነው ያሉት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የእስያ ፓሲፊክ ጉዳዮች ጄነራል ዳይሬክተር አቶ ሞላልኝ አስፋው በበኩላቸው፣ ይህ አይነቱ ፕሮግራም ህፃናትንና ወጣቶችን ከማብቃቱ በተጨማሪ የሁለቱን አገራት ታሪካዊ ግንኙነት ስለሚያጠናክር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ ያስታወቁት ዳይሬክተሩ፣ ይህ መርሃ ግብር ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን የሚያግዝ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል ነው ያሉት።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ በትምህርት፣ በኢንቨስትመንት እና በተለያዩ ዘርፎች በጋራ እየሰሩ እንደሆነም አንስተዋል።

አገራቱ ከዚህ ቀደም የኢንዶኔዥያ-ኢትዮጵያ የወጣቶች ማህበርን መመስረታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ይህም ወጣቶቹ የልምድና ልዉውጥና የስራ ዕድል እንዲያገኙ ማስቻሉ ተገልጿል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
በአባቱ መረቀ
መጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *