ኢትዮጵያ ድንገተኛ አደጋን የመከላከል አቅሟ እስከምን ድረስ ነዉ?

በሀገራችን በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሰራሽ ምክንያቶች የሚያጋጥሙ አደጋዎች በህይወትና በንብረት ላይ በርካታ ውድመት እያደረሱ የሚገኙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ከተፈጥሯዊ አደጋዎች መካከል፤ከባድ ዝናብና የጎርፍ አደጋዎች፤ የመሬት መንሸራተት፤ ድርቅ፤ የመብረቅና አውሎ ንፋስ፤ ተላላፊ በሽታዎችን ጨምሮ ሌሎችንም የሚያካትት ሲሆን በሰው ሰራሽ ምክንያት ከሚያጋጥሙት ደግሞ በዋናነት የትራፊክና የእሳት አደጋዎችን ያጠቃልላል፡፡

በሀገራችን በተለይም የትራፊክና የእሳት አደጋዎች በተደጋጋሚ የሚከሰቱ አደጋዎች ሆነው ተስተውለዋል፡፡
እነዚህ አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት፤ ቅድሚያ ከመከላል አንጻር፤ የሚደረጉት የቅድመ መካላከል ስራዎች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ኢትዮ ኤፍ ኤም የአዲስ አበባ ብሄራዊ አደጋና ስጋት ስራ አመራር ጎሚሽንን ጠይቋል፡፡

በኮሚሽኑ የአደጋ ስጋት ቅነሳና መልሶ ማቋቋም ዳይሬክተር አቶ አብርሃም አበበ፤ በዋናነት በተለያየዩ አካባቢዎች አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉና ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን በጥናት በመለየት በአካባቢው ለሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ እየሰጠን እንገኛለን ብለውናል፡፡
መረጃዎቻችን በተለይ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የብህረተሰብ ክደፍሎች የትኞቹ እንደሆኑ፤ አደጋዎችን በቅድሚያ ለመከላከል ያለንን አቅም የሚያሳዩና የግድ ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎች ከሆኑ ደግሞ የጉዳት መጠናቸውን መቀነስ የሚችሉባቸውን መፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚጠቁሙ ናቸው ብለዋል፡፡

በዚህም በወሰድናቸው የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች በርካታ ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን ማስቀረት መቻላቸውንና የተከሰቱ አደጋዎችንም እንዲሁ የከፋ አደጋ ከማድረሳቸው በፊት የተቆጣጠሩባቸው አጋጣሚዎች በርካታ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡
ተቋሙ በዚህ ደረጃ አደጋዎችን የመከላከልና የመቆጣጠር አቅም ካለው ከሰሞኑ በተለያዩ ብሄራዊ ፓርኮች ላይ ያጋጠሙትን የእሳት አደጋዎች በፍጥነት ከመቆጣጠር አንጻር መዘግየት የታየበት በመሆኑ ይሄ ለምን ሆነ? ስንል በጠየቅናቸው መሰረት፤ ይሄ ጉዳይ በዋነኝነት ከሀገራችን ኢኮኖሚዊ አቅም ጋር የሚያያዝ ነው ብለዋል ሃላፊው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ አደጋን የመከላከልና የመቆጣጠር በአንድ መስሪያ ቤት ብቻ የተወሰነ መሆነን ገልጸዉ፣ ሁሉም የመንግስትና የግል መስሪያ ቤቶች ርብርብ የሚያስፈልገው ጉዳይ እንደሆነ ነው ያነሱት፡፡

በዚህም በሃገራችን አሁን ላይ እንደተባለው በትልልቅ ፓርኮቻችን ላይ የእሳት ደጋዎች ቢከሰቱ የምናጠፋበት ሄሊኮፕተሮች የሉንም፤ በ40ና 50 ፎቆች ላይ እሳት ቢያያዝ የምናጠፋባቸው ክሪኮች የሉንም፤ ባቡሮች ከሃዲዶች ቢወጡ ወደ ሃዲዳቸው ለመመለስ የምንጠቀምባቸው ክሬኖች የሉንም ብለውናል፡፡

ከነዚህ በታች የሆኑ አደጋዎችን ግን አቅም በፈቀደ መጠን በቅድሚያ መረጃዎች ላይ ተመስርተን አደጋዎችን በመከላከል ላይ እንገኛለን ነው ያሉት፡፡
ወደፊት ደግሞ ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን አዳጋዎች የሚከተሰቱበትን ምክንያቶችና መፍትሄዎቻቸውን በተመለከተ በጥናት ላይ የተመሰረቱ መረጃዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በተቋሙ እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡

አደጋዎችን ለመቀነስ ከተከሰቱ በኋላ የሚደረገው ጥረት ሳይሆን፣ በተለይ በሰው ሰራሽ ሁኔታዎች የሚያጋጥሙ አደጋዎችን ከመከሰታቸው በፊት የሚደረገው ጥንቃቄ እጅግ ውጤታማ መሆኑን ሃላፊው አሳስበዋል፡፡
በዚህም ሰዎች በየቤታቸውና ከቤት ውጪም ሆነው በሚንቀሳቀሱበት አጋጣሚ ሁሉ፤ አደጋዎች እንደሚያጋጥሙ በማሰብ መንቀሳቀስ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

በብሄራዊ ፓርኮች አካባቢ የሚፈጠሩ የእሳት አደጋዎች የሚያደርሱት ዉድመት ዘርፈ-ብዙ በመሆኑ፤ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እነዚህን መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ መከላከሉ ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል የሚል መልእክትም አስተላልፈዋል፡፡

በጅብሪል ሙሃመድ
መጋቢት 30 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *