የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ሩሲያ በዪክሬን ያሰፈረችውን ወታደሮች እንድታስወጣ አስጠንቅቀዋል።
ሜርክል የሩሲያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን በዩክሬን ዶንባስ ክልል የሰፈሩትን ወታደሮች በፍጥነት እንዲወጡ ሲሉ መጠየቃቸውን አልጄዚራ ዘግቧል።
ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ የሩሲያ ወታደሮች በቀጠናው እየተበራከቱ መምጣታቸውን ተከትሎ፣ በሩሲያና በዪክሬን መካከል ያለው ውጥረት እየከረረ መምጣቱ ታውቋል።
እናም ሞስኮ በቀጠናው ከጠብ አጫሪነት ልትቆጠብ ይገባል ሲሉ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርክል ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ነግረዋቸዋል ተብሏል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን በበኩላቸው ዩክሬን በቀጠናው የምታደርገውን ትንኮሳ አሳሳቢ በመሆኑ ልታቆም እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ ወታደሮች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ሩሲያ ጠይቃለች ።
የኔቶ አባል አገራትም የሩሲያን ሰሞናዊ ያልተገባ እንቅስቀሴ እየተከታተልን ነዉ ብለዋል፡፡
የአሜሪካ የነጩ ቤተመንግሥት ፕሬስ ሃላፊ ጄን ፕሳኪ፣ ሩሲያ ከፈረንጆቹ 2014 ወዲህ ከፍተኛውን ጦር በቀጠናው አስፍራ እንደምትገኝና ከሰሞኑም አምስት የዩክሬን ወታደሮች መገደላቸውን አንስተዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ከሩሲያ ጋር በሚወዛገቡበት ክልል ሰሞኑን ጉብኝት እንዳደረጉና፣ ይህም ምናልባትም ሁለቱን አገራት ዳግም ወደ አስከፊ ጦርነት እንዳይከታቸው ትልቅ ስጋትን ጭሯል ነዉ የተባለዉ።
የሩሲያ መሪዎችም የዪክሬን አመራሮች ከህፃን ጨዋታቸው ይቆጠቡ ሲሉ አሳስበዋል።
ሁለቱ አገራት ከዚህ ቀደም ባደረጉት ጦርነት ከ14 ሺህ በላይ ዜጎች መሞታቸው የሚታወስ ነው።
በአባቱ መረቀ
ሚያዝያ 01 ቀን 2013 ዓ.ም











