ከዚህ በተጨማሪም 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ተጓዳኝ ምርቶችን አምርቶ ለገበያ ማቅረቡን የፊቤላ ኢንዱስትሪ ባለቤትና የቢኬጂ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ በላይነህ ክንዴ ገልጸዋል፡፡
ስምንት ሚሊየን የሚጠጋውን በአከፋፋዮች አማካኝነት ለህዝብ ማድረሱን የጠቆሙት አቶ በላይነህ ክንዴ፣ የተቀረው በመጫን ላይ ይገኛል ብለዋል።
ከአከፋፋዮች ቁጥር ማነስ ጋር በተያያዘ ምርቶችን ለተጠቃሚው የማዳረስ ችግር ተከስቶ እንደነበርም አቶ በላይነህ ተናግረዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት መንግሥት በሃገር አቀፍ ደረጃ 33 አከፋፋዮች ወደዚህ ሥራ ማስገባቱንና ከእነዚህም ውስጥ ሰባቱ ለድርጅታቸው የተመደቡ በመሆኑ የስርጭት ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ይቀረፋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ድርጅታቸው በመጀመሪያው ዙር በተፈቀደለት ውጭ ምንዛሪ 14 ሚሊየን ሊትር ድፍድፍ ዘይት ከውጪ አስገብቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ በላይነህ፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ 20 ሚሊየን ሊትር ድፍድፍ ዘይትና ሌሎች የማሸጊያ እቃዎች ከማሌዥያ አዞ ጅቡቲ ደርሶ በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
እስከአሁን የፋብሪካው የዘይት ምርቶች በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልል፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ እና በጋምቤላ ክልሎች እየተሰራጩ መሆኑን የጠቆሙት አቶ በላይነህ፣ ለአካባቢዎቹ የተመደቡ አከፋፋዮች ምርት እየወሰዱ መሆናቸውን ለኢፕድ አመልክተዋል።
ፊቤላ እስካሁን ድረስ አንድ ሊትር ከ39.05 እስከ 42 ብር ለአከፋፋዮች እያቀረበ እንደሚገኝ ያስታወቁት አቶ በላይነህ፤ ይህ ዋጋ በዓለም ላይ አንድ ሊትር ዘይት ከሚሸጥበት ዋጋ በእጅጉ ያነሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ኢትዮጵያዊያን
ሚያዝያ 04 ቀን 2013 ዓ.ም











