በትግራይ የወሲብ ጥቃት እንደ ጦር መሳሪያ አገልግሏል—የጸጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት!

ትግራይ ዉስጥ በሚደረገዉ ዉጊያ የወሲብ ጥቃት እንደ ጦር መሳሪያ ማገለግሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታዉቋል፡፡

ማርክ ሎዉኮክ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ርዳታ ቢሮ (ኦቻ) የበላይ ኃላፊ ናቸዉ፡፡

እርሳቸዉ ትናንት ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት እንዳስረዱት «በዚሕ ጦርነት የወሲብ ጥቃት እንደ ጦር መሳሪያ ማገልገሉ ምንም ጥርጥር የለዉም» ማለታቸዉን ሮይተር ዜና አገልግሎትን ጠቅሶ የጀርመን ድምጽ ሬድዮ አማረኛዉ ክፍል (DW) ጠቅሷል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ በሴቶች ላይ ስለደረሰዉ ግፍ ሲሰሙ «የአፍሪቃዉያን ሕይወት ከሌሎች ግጭት ባለባቸዉ ሐገራት ካለዉ (ሕይወት) እኩል ዋጋ የለዉም?» በማለት ምክር ቤቱ የጋራ አቋም እንዲይዝ ጠይቀዋል።

የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የጤና ጉዳይ ኃላፊ ዶክተር ፋሲካ አምደስላሴ ለሮይተርስ ዜና አገልግሎት እንደነገሩት፣ በክልሉ የሚገኙ አምስት ሆስፒታሎች በደረሳቸዉ ዘገባ መሰረት በ829 ሴቶች ላይ ጥቃት መድረሱን አረጋግጠዋል።

ሎዉኮክ እንዳሉት ሴቶቹ የተጠቁት መለዮ በለበሱ በሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ነዉ።”

ትግራይ ዉስጥ የሚደረገዉ ግጭት አሁንም እንደቀጠለ መሆኑንም አስታዉቀዋል።

ሎዉኮክ አክለዉ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ለችግረኛዉ ሕዝብ ርዳታ ለማቀበል መቸገራቸዉን ገልጠዋል።

ዓለም አቀፉ ድርጅት፣ የኤርትራ ጦር የኢትዮጵያን ግዛት ለቅቆ መዉጣቱን የሚያመለክት ምንም ዓይነት ማረጋገጪያ አለማግኘቱንም ኃላፊዉ አስታዉቀዋል።

የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ትናንት ስለትግራዩ ቀዉስ እንዲነጋገር የጠየቀችዉ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ፣ ምክር ቤቱ ከዚሕ ቀደም ባደረገዉ ተመሳሳይ ስብሰባ ይፋ መግለጫ እንዳያወጣ ሩሲያና ቻይና በማከላከላቸዉ ከፍተኛ ቅሬታ አድሮባቸዋል ብለዋል።

ትናንትም ምክር ቤቱ ሁነኛ መግለጫ እንዲያወጣ አሳስበዋል።

ይሁንና ምክር ቤቱ ትናንትም የትግራይን ግጭት የሚመለከት ይፋ የጋራ መግለጫ አላወጣም።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ አምዴ ለሮይተርስ በሰጡት መግለጫ ደረሰ የተባለዉን ሰብአዊ መብት ጥሰት መንግስታቸዉ እየመረመረ መሆኑን አስታወቀዋል።

ምንጭ ፡- DW

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
ድረ ገጻችንን https://ethiofm107.com/ ይጎብኙ::

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሚያዝያ 08 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *