ዋና አስተዳዳሪው አቶ ታደሰ ከኤትዩ ኤፍ ኤም ጋር በስልክ ቆይታን አድርገዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ ጥቃቱ ያልተገመተ ብቻ ሳይሆን እስካሁን ታይቶ የማይታወቅ ወረራ ነው ፡፡
ማህበረሰቡ ችግሮች ሲኖሩ ችግሮቹን የሚፈታበት የራሱ መንገድ ነበረው፡፡ በዚህ መንገድ አብሮ ለዘመናት ኖሯል ፡፡
አሁን ግን የግለሰቦችን ጠብ ተከትሎ በተደራጀና ንቅናቄ ባለው ሁኔታ ወደ ከፋ ሁኔታ እንዲሸጋገር ወረራን በመፈጸምም ጭምር ችግሩ እንዲከፋ ተደርጎል ነው የሚሉት ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ፡፡
በዚህ ሰበብም አጣዬ ከተማ ሙሉ ወድማለች የከተማዋ ነዋሪዎችም በስጋት ሸሽተዋል፡፡አሁን በአጣዬ እና ሸዋሮቢት የጥይት ድምጽ እየሰማን አይደለም ግን አሁንም ስጋቱ አለ ብለዋል፡፡
ለችግሩ መባባስ ሁለት ምክንያት እንዳሉት የሚናገሩት አቶ ታደሰ አንድም የጸጥታ ሀይሉ መዘግት ሁለትም ከገባ በኃላ በቂ ሀይል ይዞ አለመምጣቱ መሆኑን ነግረውናል፡፡
ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ቀጠናው ከባለፉት አመታት ወዲህ የተለየ ባህሪና ገጽታ እያሳየ መምጣቱን የሚመለከታቸው አካላት በቂ መረጃ እንዳላቸው ያነሳሉ፡፡
እነዚህ የታጠቁ የተባሉት ሀይሎች በተደራጀ እና በተናበበ ሁኔታ ጥቃቱን መፈጸማቸውንም ያነሳሉ፡፡
ከሰሜኑ የህግ ማስከበረ ጋር በተያያዘ የክልል አመራሮች ምክክር ሲያደርጉ በእነዚህ የኦሮሞ ልዮ ዞን ወረዳዎች የተለየ የፖለቲካ ተልዕኮ ያላቸው ሀይሎች እየተጠናከሩ መሆኑን ሪፖርት ይዘው ተመልሰዋል፡፡
ሪፖርቱንም ለክልሎቹም ሆነ ለፌደራል መንግስቱ እንደደረሰ መረጃ እንዳለ ነው አቶ ታደሰ የተናገሩት፡፡
መከላከያ ሚኒስትር በሰሜን ሸዋ ፣ደቡብ ወሎና ኦሮሞ ልዮ ዞን ወረዳዎች ኮማንድ ፖስት መቋቋሞን ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡
በያይኔአበባ ሻምበል
ሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም











