በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች በንፁሃን ላይ የሚደርሰዉን ጥቃት የሚያወግዙ ሰልፎች ዛሬም ቀጥለዋል፡፡

በጎንደርና እንጅባራ ከተሞች በዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ዘር ተኮር ጭፍጨፋ እና መፈናቀል የሚያወግዙ ሰልፎች እየተካሄዱ መሆናቸዉን የአካባቢዉ ነዋሪዎች ለኢትዮ ኤፍ ኤም አስታውቀዋል፡፡

በባህር ዳር ከተማም በዛሬዉ እለት ሰልፎች እንደቀጠሉና የስራ ማቆም አድማዎች እንዳሉም ሰምተናል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብር ብርሃን ከተማም፣ በትናትናዉ ዕለት የተጀመረዉ የተቃዉሞ ሰልፍ ዛሬም መቀጠሉን ነዋሪዎቹ ነግረዉናል፡፡

በሰልፎቹ ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ ሞትና መፈናቀል ይቁም የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት የዜጎች ደኅንነት ሊያሳስበው ይገባል የሚሉ መፈክሮችን በማስተላለፍ ላይ ናቸዉ፡፡

ሰሞኑን በሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙት አጣዬና የሸዋሮቢት ከተሞች፣ በንፁሃን ላይ በደረሰዉ ጥቃት ቁጥራቸዉ በዉል ያልታወቁ ንጹሃን ሰዎች መገደላቸዉንና፣ ቤት ንብረታቸዉ መውደሙንም የአካባቢዉ ተጎጂዎችና የዞኑ አስተዳደር መናገራቻዉ ይታወሳል፡፡

ይህንን ጥቃት በማዉገዝ በአማራ ክልል የሚገኙ ዞኖችና ከተሞች የንጹሃንን ግድያና መፈናቀል የሚያወግዙ ሰልፎችን አካሂደዋል፤ አሁንም በማካሄድ ላይ ናቸዉ፡፡

የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲም በትናትናዉ ዕለት ባወጣዉ መግለጫ፤ እነዚህ ጥያቄዎች ተገቢና ተቀባይነት አላቸው ብሎ እንደሚያምንና፣ የአማራ ህዝብ ሞትና መፈናቀል በዘላቂነት እንዲቆም ይታገላል ብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአማራ ህዝብ ሞትና መፈናቀል እጃቸው ያለበትን ማናቸውንም የጥፋት ሀይሎች፣ ለህግ ለማቅረብና አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ቁርጠኛ ስለመሆኑም ፓርቲዉ በመግለጫዉ አመላክቷል፡፡

በአባቱ መረቀ
ሚያዝያ 14 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *