የሱዳን የጦር ሃይል የያዘዉን መሬት ለቆ ሳይወጣ የበልጉና ክረምቱ ወቅቶች እየተቃረቡ በመምጣቸዉ እነዚህ አርሶ አደሮች ለግብርናቸዉ የማይመለሱ ከሆነ ከእርሳቸዉ አልፎ ለአገሪቱም ትልቅ ራስ ምታት እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡
በባህር ዳር ዩንቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና የአለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ አበበ ይርጋ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ የሱዳን ጦር ድንበር መጣሱ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን አርሶ አደሮችና ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳ ነዉ ይላሉ፡፡
የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ከመድፈሩ ባለፈ የሁለቱ አገራት ኢኮኖሚ እንዲጎዳ አድርጎታል ያሉት አቶ አበበ፤ በቀጣይ የኢትዮጵያ መንግስት ብዙ የቤት ስራዎች ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን ጦርነት አማራጭ ባይሆንም ኢትዮጵያ ግን የዲፕሎማሲ ስራዎችን በትኩረት ልትሰራ እንደሚገባም ምሁሩ አሳስበዋል፡፡
ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለዉ ስፍራ ነዉ፤ አሁን ላይ የሱዳን ወታደራዊ ሃይል በቁጥጥር ስር ያዋለዉ የኢትዮ ሱዳን ድንበር፤ በተለይም ሰሊጥ ፤ጥጥና ሌሎችም ምርቶች በስፋት የሚመረቱባት ይህ ቦታ የአገሪቱን የግብር ዘርፍ ከማገዙ ባለፈ ለበርካታ ኢትጵያዉያን የስራ እድል እንደፈጠረ ይነገራል፡፡
ኢትዮጵያ የዉጭ ምንዛሬ ችግሮቿን በብዛት የምትቀርፈዉ በቅባት እህሎች እንደሆነ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ የሚያመላክት ሲሆን ከ30 በመቶ በላይ የሚመረቱት እነዚህ ቅባቶች በሰሜን እና በሰሜን ምእራብ የአገሪቱ ክፍሎች ነዉ፡፡
ያ ማለት ደግሞ አሁን በሱዳን ጦር ስር የሚገኘዉ አካባቢም የአንበሳዉን ድርሻ ይወስዳል፡፡
ይሁን እንጂ ከባለፈዉ ጥቅምት ወር ጀምሮ የሱዳን ወታደራዊ ሃይል የኢትዮጵያን ድንበር በሃይል ጥሶ በመግባቱ ኢትዮጵያዉያን ዜጎች በብዙ ድካምና እንግልት ያረሱትንና ያለሙትን ሰብል አቃጥሏል፤ አርሶ አደሮችንም ለስደት፤ ለስቃይና እንግልት ዳርጓቸዋል፡፡
ታዲያ የባለፈዉ ጉዳት ሳያንስ እነዚህ አርሶ አደሮች ተጨማሪ ችግር ዉስጥ ለመግባት የተቃረቡ ይመስላል ፡፡
ለመሆኑ ኢትዮጵያ ይህን ለም መሬትና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ያለዉን ቦታ ከሱዳን እጅ ለማስወጣት ምን የተለየ ነገር አስባ ይሆን የሚለዉ የበርካቶች ጥያቄ ነዉ፡፡
ከዚህ ቀደም ችግሩን ለመፍታት ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ እንደምትራ በተደጋጋሚ ስትገልፅ ቆይታለች፡፡
አሁንም ኢትዮጵያ ለድንበር ዉዝግቡ ዲፕሎማሲን ትመርጣለች ነዉ ያሉት የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፡፡
የሱዳን ጦር በሌሎች አካላት ግፊት አማካኝነት በሁለቱ አገራትና በቀጠናዉ ግጭቶችን ለመፍጠር እየሰራ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን ይህን በፍጹም አንደማትቀበለዉ አስታዉቃለች፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን የሱዳን መንግስት በህዳሴ ግድብም ሆነ በድንበር ጉዳይ የሌሎችን አጀንዳ ማፅፈጸም አይኖርባትም ነዉ ያሉት ቃል አቀባዩ፡፡
ባጠቃላይ የኢትዮ ሱዳንን ድንበር ጉዳይ በፍጥነት ምላሽ እንዲገኝ በማድረግ የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችንና በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ እያሳደረ ያለዉን ጉዳት ለመቀነስ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነዉ፡፡
በአባቱ መረቀ
ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም











