ኢትዮጵያ የሶስትዮሽ ድርድሩ እንዲቀጥል እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረገውን የሶስትዮሽ ድርድር በቅርቡ እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላት የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገልፀዋል።

ቃል አቀባዩ ሳምንታዊ መግለጫ በመስጠት ላይ ሲሆኑ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ የሶስትዮሽ ድርድሩ በቅርቡ እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ፅኑ እምነት አላት ብለዋል።

ኢትዮጵያ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር የሆነችው ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ድርድሩ እንዲጀመር ትሰራለች የሚል እምነት እንዳላትም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረት ካላት አክብሮት አንፃር ድርድሩ በህብረቱ እንዲቀጥል ፅኑ አቋም እንዳላትም አንስተዋል።

ሱዳን እና ግብፅ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ወደ አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ለመውሰድ ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ በኢትዮጵያ በኩል ግን ተቀባይነት እንደሌለው በተደጋጋሚ ተገልጿል ።

ከዚህ በተጨማሪም ቃል አቀባዩ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በሚሲዮኖቹ አማካኝነት በሳምንቱ የተሰሩ ስራዎችን በመግለጫቸው አንስተዋል።

በተለይም የአፍሪካ ሩሲያን የትብብር መድረክ ኢትዮጵያ ለማዘጋጀት ፋላጎት እንዳላት ለሩሲያ መንግስት ገልፃለች ተብሏል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
በአባቱ መረቀ
ሚያዝያ 19 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.