በበዓሉ ወቅት የኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ችግር እንዳያጋጥም እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

ከባዕሉ ዋዜማ ምሽት 4 ሰዓት ጀምሮ እስከ በዓሉ ምሽት 4 ሰዓት ድረስ ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች በስተቀር የኤሌክትሪክ ሃይልን በብዛት የሚጠቀሙ ድርጅቶች ከዋናው የኃይል ቋት (ግሪድ) እንዳይጠቀሙ አሳስቧል፡፡

ተቋሙ የላከልን ሙሉ መግለጫ የሚከተለዉ ነዉ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2013 ዓ.ም የትንሳዔ በዓል ወቅት ሊኖር የሚችለውን የኃይል መቆራረጥና መዋዥቅ ችግር ለመፍታት የተለያዩ የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

ተቋሙ በበዓሉ ዋዜማና በዕለቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ሳይቆራረጥና ሳይዋዥቅ ለተጠቃሚው ለማቅረብ እንዲሁም ችግሩ ከተከሰተም በተገቢው መንገድ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎች በማከናወን ላይ ሲሆን፤ በዋናነት በተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ የሚስተዋልባቸውን አካባቢዎች በመለየት በመካከለኛና በዝቅተኛ መስመሮች ላይ ጭነት የማመጣጠንና ሌሎች የቅድመ-መከላከል ስራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡

ወቅቱ የረመዳን ፆም እንደመሆኑ መጠን ያልተቆራረጠ ኃይል ለማቅረብ እንዲቻል መሰል ሥራዎች አስቀድመው የተጀመሩ ሲሆን፣ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረው ጫና ለመቀነስ ተከታታይነት ያላቸው የመልሶ ግንባታና የማሻሻያ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በጋራ በመሆን ከኃይል ማመንጫ ጀምሮ እስከ ማስራጫ መስመሮችና ትራንስፎርመሮች ድርስ እንዲሁም በዝቅተኛ መስመሮች ላይ ብልሽቶች ሲያጋጥሙ በአፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚችል ስታንድባይ ኮሚቴ በየደረጃው በሚገኙ አደረጃጀቶች በኩል በማቋቋም ወደ ስራ ገብተዋል፡፡

ሆኖም መሰል ዝግጅቶች ቢደረጉም አሁንም መቆራረጥ ሊያጋጥም ስለሚችል ከስሚንቶ ፋብሪካዎች በስተቀር የድንጋይና እህል ወፍጮ፣ የፕላስቲክ፣ የጨርቃ ጨርቅ፣ የብረታ ብረት፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የኬሚካልና ሌሎች ዝቅተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በበዓሉ ዋዜማ ሚያዝያ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡00 እስከ በዓሉ ዕለት ምሽት 4፡00 ድረስ ከዋናው የኃይል ቋት (ግሪድ) ኤሌክትሪክ ሙሉ ለሙሉ እንዳይጠቀሙና ሊፈጠር የሚችለውን ጫና ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ተቋሙ እንደሁልጊዜው ይጠይቃል።

የቅድመ ክፍያ ተጠቃሚ ደንበኞች በበኩላቸው በዓሉ ሲደርስ የሚኖረውን አላስፈላጊ እንግልት ለማስቀረት እንዲችሉ ከወዲሁ የሚበቃቸውን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይል አስቀድመው እንዲገዙ /ካርድ እንዲሞሉ/ እናሳስባለን፡፡

ደንበኞችም በቤት ውስጥ የሚገለገሉባቸውን የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶች ኃይል ቆጣቢና ለአደጋ የማያጋልጡ መሆን ይገባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ኃይል ጭነት በማይበዛበት ሰዓታት በተለይ ከምሽቱ 4፡00 እስከ ንጋቱ 11፡00 ባሉት ጊዚያት ቢጠቀሙ የተሻለ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማግኘት ባለፈ የኤሌክትሪክ መቆራረጥንም ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል በሚቋረጥበት ጊዜ የጥገና ስራ ለማከናወን የተቋማችንን መታወቂያ የያዙ የቴክኒክ ባለሞያዎቻችን በተለያዩ አካባቢዎች ለስራ ጉዳይ እንደሚንቀሳቀሱ ህብረተሰቡ ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግም ይኖርበታል፡፡

ይሁንና የተቋሙ የጥገና ሰራተኞች በመምሰል መሠረተ ልማቱ ላይ ስርቆትና ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ አካላት ሊኖሩ ስለሚችሉ፤ ህብረተሰቡ ይህንን ከወዲሁ ተገንዝቦ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መስመሮችን በመጠበቅ እንዲተባበርና እኩይ ተግባራት ሲገነዘብም ለሚመለከተው የህግ አካላትና ለተቋሙ ማሳወቅ ይገባዋል፡፡

በመጨረሻም ድንገት የኤሌክትሪክ አደጋ ቢያጋጥም፣ ተቋሙን የሚመለከቱ ሌሎች መረጃዎች ለመጠየቅ እንዲሁም ጥቆማዎችና አስተያይቶች ለማቅረብ ወደ አቅራቢያቸው የሚገኝ የአገልግሎት መስጫ ማዕከል በአካል በመሄድ ማሳወቅ ወይም ወደ 905 ነፃ የጥሪ ማዕከል መደወል እንደሚያስፈልግ እንጠቁማለን፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሚያዝያ 20 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.