በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት በምስረታ ሂደት ላይ የሚገኘው ሂጅራ ባንክ፣ ዋና መስሪያ ቤቱን በአዲስ አበባ ደንበል ሲቲ ሴንተር ፈት ለፊት በገዛው ህንፃ ላይ አድርጓል።
በምስረታ ላይ ሆኖ የራሱን ህንፃ መግዛት የቻለ የመጀመሪያው ባንክ ነውም ተብሏል።
የባንኩ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት ቀኖ እንዳሉት፣ ባንኩን ለመመስረት አስፈላጊ የሆኑ የቅድሚያ ስራዎች አብዛኞቹ መጠናቀቃቸውን ገልፀዋል።
በዚህም ከብሄራዊ ባንክ ፈቃድ መውሰድ ፣አክሲዮን የመሸጥ፣ የመስራች ባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ፣ የባንኩን ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት መሰየምና ባንኩ የሚተዳደርበትን ደንብና መመሪያዎችን ማፅደቅ እስካሁን ድረስ የተሰሩ ስራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ባንኩ በ2 ወራት ጊዜ ውስጥ ስራ እንደሚጀምር የገለፁት አቶ ዳዊት፣ አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችለውን እና ለባንክ ስራ መስራት የሆነውን የኮር ባንኪንግ ሲስተም ለመግዛት ቀሪ ስራዎች በመኖራቸው ነው ብለዋል።
በቅርቡ የብሔራዊ ባንክ ያወጣው የመመስረቻ መነሻ ካፒታል ወደ 5 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ መደረጉ እንደማያሰጋቸው እና አሁን ቃል የተገባው 1.2 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል፡፡
የመመስረቻ ካፒታል መጠኑን ለማሟላት የ7 አመት ጊዜ ስለሚኖረን እንደሚያሟሉ ያላቸውን እምነት ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ባንኩ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖችን ጨምሮ ከወለድ ነፃ የሆነ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ለሚፈልጉ ኢትዮጵያዊን ሁሉ ክፍት ነው ብለዋል።
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
በጅብሪል ሙሃመድ
ሚያዝያ 21 ቀን 2013 ዓ.ም











