ከመተከል ዞን ተፈናቅለው በቻግኒ ከተማ እና በጓንጓ ወረዳ ተጠልለው የሚገኙ ቁጥራቸው ከ77ሺ በላይ የሆኑ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ምዕራብ ጎጃም, ደቡብ ጎንደርና አዊ ዞን እንዲዘዋወሩ የቀረበላቸውን ሃሳብ ውድቅ አደረጉት።

ከትላንትና በስቲያ ከአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ያደረጉት ተፈናቃዮች እንዳሉት ወደ ቀድሞ ቀያችን መተከል ዞን ፓዊ እንጂ ወደ ሌሎች ቦታዎች መሄድ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል ፡፡

ባለፈው ጳጉሜ 2012 በመተከል ዞን በነበረው ቀውስ ከቀዬያቸው ከተፈናቀሉ ከ7 ወራት ጊዜ በላይ እንደሆናቸው የተናገሩት ተፈናቃዮቹ የክልሉ መንግስትም ለ3 ወራት ብቻ ተብሎ ቻግኒ ከተማ እንዲጠለሉ ቢደረግም የአማራ ክልል መንግስት ቃሉን አልጠበቀም ሲሉ የቻግኒ ከተማ ከንቲባ አቶ ደምሰው ይስማው ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

በሶስት ወራት ጊዜ ወደ ቀያቸው ትመለሳላችሁ ተብለው የነበሩት ተፈናቃዮቹ አሁን የተጠለሉበት የሸራ ድንኳን ክረምትን ታሳቢ ያደረገ ባለመሆኑም እና ከሰሞኑ በሀገሪቱ ያለው የበልግ ዝናብ የተፈናቃዮቹን መጠለያ ድንኳን እያፈረሰባቸው እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የተፈናቃዮቹ መጠለያ ድንኳን ዝናቡን ሊከላከለው ባለመቻሉ ችግር እንዳጋጠመ ያመኑት አቶ ደምሰው በአሁኑ ሰአትም መጠለያ ጣቢያዎች ተጨማሪ ሸራ እያቀረብንላቸው ነው ብለዋል፡፡

በዘላቂነት ወደ ቀያቸው ከመመለስ ባሻገር በክልሉ ወደ ምዕራብ ጎጃም ፣ደቡብ ጎንደርና አዊ ዞን ለማዘዋወር የቀረበውን ሃሳብ ተፈናቃዮቹ ሊቀበሉት እንዳልቻሉ ከንቲባው ነግረውናል፡፡

እነኚህ ተፈናቃዮች በቶሎ ወደ ቀዬያቸው ካልተመለሱ አልያም ሌላ መፍትሄ ካልተሰጣቸው መጪው የክረምት ወራት እንደሚያሰጋቸው ቅሬታ ማቅረባቸውን ኢትዮ ኤፍ ኤም ዘግቦ ነበር፡፡

ከተማዋ ከብዷታል ወይ? ስንል ለአቶ ደምሰው ጠየቅን

እስካሁን የምንችለውን ሁሉ አድርገናል አሁን ግን ተላላፊ በሽታ ቢፈጠርና ሰርጎ ገቦች የጸጥታ ችግር ቢፈጥሩ በቂ የጸጥታ ሀይል ስለሌለን ወደ ሌሎች አካባቢዎች መዘዋወራቸው ዘላቂ መፍትሄ እስኪገኝ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
በመቅደላዊት ደረጀ
ሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *