“የእኛ በምርጫው መሳተፍ ምርጫው አሳታፊ ስለመሆኑ ማሳያ ሊሆን ስለሚችል በአስቸኳይ እልባት እንዲሰጠን” ሲል ኦነግ ጠየቀ

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ውድቅ ተደርጎበት የነበረው በአቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው ኦነግ፤ በምርጫው መሳተፍ ብንችል ምርጫው አሳታፊ ስለመሆኑ ማሳያ ሊሆን ስለሚችል ምርጫ ቦርድም ሆነ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ይስጠን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በአቶ አራርሶ ቢቂላ የሚመራው ኦነግ ቃል አቀባይ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት ምርጫ ቦርድ የጠቅላላ ጉባኤውን ውሳኔ ተቀብሎ በምርጫ መሳተፍ እንዲችሉ በማለት ከፍተኛው ፍርድ ቤት ያስተላለፈውን ዉሳኔ ቦርዱ በአፋጣኝ እንዲያስፈጽም ውሳኔ መስጠቱን አስታውሰዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ መጋቢት 04 ቀን 2013 ዓ.ም የአመራር አባላቱ ያደረጉትን ጠቅላላ ጉባኤ ሁሉንም አመራሮች ያላሳተፈ በሚል እንደማይቀበለው ማሳወቁ የሚታወስ ነው፡፡

ቃል አቀባዩ አቶ ቀጀላ “እኛ ወደ ምርጫው መመለሳችን ምርጫው አሳታፊ ስለመሆኑ ማሳያ ሊሆን ይችላል” ባይ ናቸው፡፡

ምርጫ ቦርድ የፍርድ ቤቱን ዉሳኔ በፍጥነት ተግባራዊ በማድረግ በ6ኛ ብሔራዊ ምርጫ መሳተፍ እንዲችሉ ጠይቀዋል፡፡

በመላው ሃገሪቱ በ11 ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች ሲካሄድ የቆየው የመራጮች ምዝገባ ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳውቁ የሚታወስ ነው፡፡

“ባለቀ ሰአትም ቢሆን ቦርዱ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመመልከት ፈጣን ምላሽ ከሰጠን እና ለጥቂት ቀናት ቢሆን የተወሰኑ የመገናኛ ብዙሃንን እንድንጠቀም ቢደረግ፣ ከምርጫው ተሳትፎ በዘለለ ማሸነፍ እንችላለን ”ብለዋል፡፡

“ህዝቡ ማንን እንመረጥ እያለ ነው ፣ አንድ ፖርቲ ብቻ እንዴት ይቀርባል ? አማራጭ በሌለበት እንዴትስ አድርገን አንድ ፖርቲ ብቻ እንመርጣለን እያለ ስለሆነ በተለይ በኦሮሚያ አካባቢዎች ገዢው ፖርቲም ሆነ መንግስት ነገሩን ከግምት አስገብቶ በአፋጣኝ ምላሽ እን ዲሰጠን እንጠይቃለን” ሲሉ ቀጀላ ተናግረዋል፡፡

“እርግጥ ፍርድ ቤት በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ መሰረት ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚል ውሳኔ ሰጥቷል ፡፡ ጠቅላላ ጎባኤው ከወሰናቸው መካከል ደግሞ ወደ ምርጫ መግባት አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ‘የቀድሞው ሊቀመንበር ’ ወደ ምርጫው አንገባም ብለው አስቀድሞ አውጆ የነበር መሆኑን አስታሰው መጋቢት 04 ቀን በተደረገው ጠቅላላ ጉባኤው ግን ወደ ምርጫ መግባቱ አስፈላጊ መሆኑን ታምኖበት ነበር“ ብለዋል ቀጀላ፡፡

በዚያ ውሳኔ መሰረት ምርጫውን ለማድረግ በቀሩ ጊዜያት እጩዎቻችን እንዲመዘግቡልን እና በምርጫውን እንድንሳተፍ ቢደረግ ምርጫውም የበለጠ አሳታፊ ይሆናል ሲሉ አቶ ቀጀላ ለጣቢያችን ተናግረዋል ፡፡

በውስጣዊ ችግር ለሁለት የተከፈለው ኦነግ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ፓርቲዎች ውስጥ ይገኝ ነበር፡፡

በያይኔአበባ ሻምበል
ግንቦት 06 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *