በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት እና ስማቸው ባልተጠቀሰ “ታጣቂ ቡድን” መካከል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ባወጣው መረጃ መሰረት ስምምነቱ የተካሄደው በታጣቂ ቡድኑ በኩል የሚነሱ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፍትሄ ለመስጠት የተሃድሶ ስልጠና እየወሰዱ ከሚገኙ አባላት ጋር ነው።

በስምምነት ሰነዱ ውስጥ ከተካተቱ ዋና ዋና አጀንዳዎች መካከል፤ ከእነዚህ ሃይሎች አባላት መካከል አቅምና የትምህርት ደረጃቸውን በማየት በክልል ደረጃ 2 ፣በዞን ደረጃ 3 እና በወረዳ ደረጃ ደግሞ 4 የሃላፊነት ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ ፣የከተማ የቤት መስሪያ ቦታ፣ የገጠር የእርሻ መሬት እንዲያገኙ ማድረግ፣ሴቶችን በማካተት በተለያዩ ማህበራት እንዲደራጁ ማስቻል፣በተማሩበት የሙያ መስክ እንዲመደቡ ማድረግ፣ ከአሁን በፊት ልምድ ያላቸውን ሰዎች በክልሉ ውስጥ ባሉ የጸጥታ መዋቅሮች መመደብ እና የብድር አገልግሎት መስጠት የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው።

የመግባቢያ ሰነዱን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዝዳንት አሻድሊ ሀሰን እና የታጠቀው ቡድን ተወካይ ጀግናማው ማዋንግ ተፈራርመዋል፡፡

በስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት አሻድሊ የክልሉ መንግስት የመግባቢያ ስምምነቱን ያለምንም መዘግየት ይተገብራል ብለዋል፡፡

አተገባበሩን ለማመቻቸት በክልሉ የመተከል ዞን ዋና ከተማ በሆነው ግልገል በለስ ከተማ በሶስት የታጠቁ ቡድን አባላት ጊዜያዊ ጽህፈት ቤት ተቋቁሟል፡፡

አቶ አሻልዲ አክለውም የመግባቢያ ሰነዱ አተገባበር የክልሉ መንግስት የህግ የበላይነት በሚፈቅድለት መጠን እንደሚመቻች እና የተሃድሶ ስልጠና የሚወስዱ ስማቸው ያልተጠቀሰ የታጣቂ ቡድን አባላት የቀሩትን አባላት ለማምጣት የሰላም አምባሳደር ሆነው ማገልገል እንደሚገባቸው ተናግረዋል ፡፡

በመግባቢያ ሰነዱ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሰራዊት የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ እና የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ምክትል ሀላፊ ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ወልዲ እንዲሁም ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የታጠቀው ቡድን አባላት ተገኝተዋል ብሏል ቢሮው፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ግንቦት 11 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *