የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ10 ወራት 569,767 ሜትሪክ ቶን ምርት በ36 ቢሊየን ብር አገበያየ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2013 በጀት ዓመት አስር ወራት 569,767 ሜትሪክ ቶን ምርት በ36.5 ቢሊየን ብር አገበያይቷል፤ አጠቃላይ ግብይቱ የእቅዱን በመጠን 101 በመቶ በዋጋ 107 በመቶ ይሸፍናል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከተገበያየው ምርት መጠን ውስጥ ውስጥ ቡና 35 በመቶ፣ ሰሊጥ 32 በመቶ፤ አኩሪ አተር 14 በመቶ፤ ቀይና ዥንጉርጉር ቦሎቄዎች ሰባት በመቶና ነጭ ቦሎቄ አምስት በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡

በእነዚህ 10 ወራት 201,401 ቶን ቡና ለግብይት ቀርቦ በ21.8 ቢሊየን ብር፤ እንዲሁም 183,299 ቶን ሰሊጥ በ9.7 ቢሊየን ብር ለመገበያየት በቅቷል።

ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትን የመዘርጋት አገራዊ ተልዕኮ የያዘው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግና የአገራችንን የወጪ ንግድ ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

እንዲሁም ዘይት አምራች የግብርና ምርት አቀነባባሪ ኢንዱስትሪዎች ለግብዓት የሚጠቀሙበትን አኩሪ አተር ከዘመናዊ ግብይት ስርዓቱ ማግኘት የሚችሉበት አዲስ የገብይት መስኮት ከተከፈተበት ከጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓም አንስቶ 25 አቀናባሪዎች 39,886 ሜትሪክ ቶን ምርት በ888 ሚሊየን ብር ማገበያየት ተችሏል።

ይህም የውጭ ምንዛሪ በማዳን ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተደራሽነቱን ለማስፋት በሚዛን አማንና ቴፒ ተጨማሪ ሁለት የምርት መቀበያ ማእከላትን ከፍቷል። የክልል የኤሌክትሮኒክ ግብይት ማዕከል ለመክፈት በተያዘው ዕቅድ መሰረት በጎንደር አዲስ ማዕከል ተከፍቶ ስራ ጀምሯል፡፡

በቅርቡም አዳማና ጅማ ተጨማሪ የኤሌክትሮኒክ የግብይት ማዕከላት ተመርቀው ሥራ ይጀምራሉ ሲሉ ለጣቢያችን በላኩት መግለጫ አስታቀዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ግንቦት 11 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.