አሜሪካ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ባለስልጣናት ላይ የጣለችው ማእቀብ የአፍሪካ ቀንድን በእጅጉ ይጎዳዋል ተባለ፡፡

አሜሪካ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የጣለችው ማእቀብ የአፍሪካ ቀንድ በእጅጉ እንደሚጎዳው በአፍሪካ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን አሳስበዋል፡፡

ሀገሪቷ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራ አንቶኒ ብሊከን በኩል በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ከፍተኛ አመራሮች ላይ የጉዞ እገዳ መጣሏ አስታውቃለች፡፡

በአፍሪካ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን እንደገለጹት አሜሪካ የጣለችው የኢኮኖሚ እንዲሁም በሰላም እና የደህንነት ማእቀብ እነዚህን ሀገራት ብቻ ሳይሆን ቀጠናው ጭምር በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳዋል ብለዋል፡፡

ላውረንስ ሲያክሉም አሜሪካ ለበርካታ አመታት ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት ትብብር መልካም የሚባል ነበር አሁን ይህ ውሳኔ ሀገራቱ የነበራቸውን ግኑኝነት የሚሸረሽር ነው ብለዋል፡፡

የጆ ባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያ በቀጠናው እየተጫወተች ያለውን ሚና ከግንዛቤ ያስገባ ውሳኔ አላሳለፈም ይህም ተግባራቸው ለቀጠናው ያላቸው ግዴለሽነት ያሳያል ነው ያሉት፡፡

ይህ ማእቀብ የሚጸና ከሆነ ቀጠናው የሽብርተኞች መፈንጫ መሆኑ አይቀርም፣ በመሆኑም የጆ ባይደን አስተዳደር ውሳኔውን በድጋሚ ማጤን እንዳለበት ነው ላውረስ ፍሪማን በትንታኔያቸው ያስቀመጡት፡፡

አሜሪካ በአፍሪካ ሀገራት ላይ የምትጥላቸው የተለያዩ ማእቀቦች ለአፍሪካ ያላትን ግዴለሽነት ፍንትው አድርጎ የሚገልጽም ነው ብለዋል፡፡

ከባራክ ኦባማ ዘመን አንስቶ የሪፐብሊካን እና የዲሞክራት ፓርቲ ፕሬዝዳንቶች በአፍሪካ ሀገራት ላይ የሚያሳለፉት ውሳኔ እጅጉን አደገኛ እና የአህጉሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
ሄኖክ ወልደ ገብርኤል
ግንቦት 16 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *