ሃገር እያጋጠማት ካለው ፈተና እንድትወጣ ሁሉም ሰላምን እንዲያስቀድም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ማትያስ ጥሪ አቀረቡ፡፡

በኢትዮጵያ ላሉት ችግሮች ሁሉ መፍትሄው ሰላም በመሆኑ ሁሉም ለሰላም ሲል አስፈላጊውን ዋጋ መክፍል እንዳለበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርሰቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጥሪ አቀረቡ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከዛሬ ጀምሮ መካሄድ ላይ ይገኛል።

በጉባኤው የመክፈቻ መርሃ ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርሰቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በሰው ልጆች ላይ ከበድ ያለ ፈተና እየተከሰተ በመሆኑ ሁሉም ሊጸልይ ይገባል ብለዋል፡፡

የቤተ-ክርስቲያኗ ገዳማትና አድባራት፣ መነኮሳትና ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና ወጣቶች እንዲሁም ምዕመናን ፈተና ላይ ሲወድቁ ቅዱስ ሲኖዶሱ በቀጥታ የሚመለከተው በመሆኑ ለመፍትሄው ሊሰራ ይገባልም ነው ያሉት።

በሀገሪቷ በተለያዩ አከባቢዎች በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ጉባኤው በጸሎት፣ በማስታረቅ፣ በቁሳቁስና በመጠለያ እንዲሁም በምግብና መጠጦች ድጋፍ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ላሉት ችግሮች ሁሉ መፍትሄው ሰላም በመሆኑ ሁሉም ለሰላም ሲል አስፈላጊውን ዋጋ መክፍል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘላቂና ዋስትና ያለው ሰላም ለማምጣት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በውይይት፣ በመነጋገርና በመግባባት ለጋራ ሰላም ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ሠላም የህልውና ጥያቄ መልስ በመሆኑ ሁሉም በጋራ እንዲቆምም ፓትሪያርኩ ጥሪያቸውን አርበዋል።

በጉባኤውም በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገር የሚገኙ የሲኖዶሱ አባላት የተገኙ ሲሆን የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትሪያርክ ብጽእ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የመክፈቻ ንግግርም አድርገዋል፡፡

እንደ ሃገርም ሆነ እንደ ቤተክርስቲያን የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ወደ አምላክ መቅረብና በትጋት መጸለይ እንደሚገባ አቡነ ማትያስ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ግንቦት 18 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *