የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) 127 አባላትና ደጋፊዎቹ በኮንሶ ዞን እንደታሰሩበት ገለጸ፡፡

ፓርቲዉ ቅስቀሳ በሚያደርግባቸዉ የተለያዩ አካባቢዎች ከቅስቀሳ በኋላ አባላትና ደጋፊዎቹ ለእስርና ወከባ እየተዳረጉት መሆኑን ተናግሯል፡፡

በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የምረጡኝ ቅስቀሳ እያደረገ እንደሚገኝ የገለጸዉ ኢዜማ፣የምርጫ ቅስቀሳዉ ከተካሄደ በኋላ አባላትና ደጋፊዎቹ ለእስርና ወከባ እንደሚዳረጉ የፓርቲዉ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ ዘላለም ወርቅአገኘሁ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

አቶ ዘላለም እንዳሉት በትናንትናዉ እለት ብቻ በኮንሶ 127 የፓርቲዉ አባላትና ደጋፊዎች መታሰራቸዉን በስም ዝርዝር የተደገፈ ሪፖርት ደርሶናል ብለዋል፡፡

ባሳለፍነዉ ሳምንትም በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ ላይ ተመሳሳይ ችግር ማጋጠሙን የገለጹት አቶ ዘላለም፣የፓርቲዉ አመራሮች ቅስቀሳ ባደረጉባቸዉ አካባቢዎች በአብዛኛዉ ይህ ችግር እንደሚከሰት ነግረዉናል፡፡

ኢዜማ እነዚህን ችግሮች ወደ መገናኛ ብዙሃን ያልወሰደዉ ለአባላትና ደጋፊዎቹ ስለማይጨነቅ ሳይሆን ወደተለመደዉ ሂደት መግባት የለብንም በሚልና ሂደቱን ላለማጨለም በማሰብ ነዉ ብለዋል፡፡

“የምናደርገዉ የምርጫ ቅሰቀሳ ሰላማዊና፣ የምርጫ ሕጉን የተከተለ ቢሆንም አባላትና ደጋፊዎቻችን ግን ከእስርና ወከባ አላመለጡም፤ ገዥዉ ፓርቲ በምርጫ ቢሸነፍ ስልጣን የማስረከብ የስነ-ልቦና ዝግጅት ያለ አይመስለኝም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“ታችኛው የመንግስት እርከን ላይ ያሉ ሃላፊዎችም ቢሸነፉ የመጨረሻቸዉ እንደሚሆንና የተለመደ የቂም በቀል ሂደት ይኖራል የሚል ፍራቻ ያለባቸዉ ይመስለኛል፤ይህ ስህተት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል” ብለዋል፡፡

በአባላትና ደጋፊዎቹ ላይ የሚደርሱ እስራትና ማዋከቦችን ለምርጫ ቦርድና ለሰብአዊ መብት ኮሚሽን በተደጋጋሚ ማሳወቁን የገለጸዉ ፓርቲዉ፣ ተቋማቱ የአቅም ዉስንነት ካልሆነ በስተቀር የሚሰጡት ምላሽ መልካምና ተስፋ ሰጭ መሆኑን ገልጿል፡፡

በዚህም በትናንትናዉ እለት ለእስር የተዳረጉ አባላቶችና ደጋፊዎቹን ጉዳይ በስም ዝርዝር አስደግፎ ለምርጫ ቦርድ መላኩን የገለጸዉ ኢዜማ፣ ችግሮች መፍትሄ የሚያገኙበትን መንገድ እየተከታተለ እንደሚገኝ አስታዉቋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
በሙሉቀን አሰፋ
ግንቦት 18 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.