በእንጦጦ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ የሚገኘዉ ጥቅጥቅ ደን ተመንጥሮ ለኤሌክትሪክ ኃይል የሰብስቴሽን ግንባታ ሊዉል በመሆኑ የሚመለከተዉ አካል ያስቁምልን ሲል የቅርስ ባለደራ ማህበር ጠየቀ

በፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ የሚገኘዉና በማህበሩ ይዞታ ስር አገር በቀል እፅዋት የሚገኙበትን ጥብቅ ደን ስፍራን መንጥሮ የሰብስቴሽን ግንባታ አካሂዳለሁ በማለቱ የሚመለከተዉ አካል እንዲያስቆመዉ ሲል ቅሬታዉን ተናግሯል፡፡

ጥቅጥቅ ደኑን ማህበሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በአገር በቀል እፅዋት ለመሸፈን ሲታገል እንደነበር የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ መቆያ ማሞ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

ቦታዉ በርካታ አገር በቀል እፅዋቶችን የያዘና የቱሪስት መዳረሻ ሊሆን የሚችል በመሆኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ቦታዉን መንጥሮ ሰብስቴሽን ግንባታ ማካሄድ እንደሌለበት ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ሁሉ ብናሳዉቅም አሁን ድረስ አዎንታዊ ምላሽ አልተሰጠንም ብለዋል፡፡

መንግስት አረንጓዴ አሻራ እናሳርፍ እያለ ሕብረተሰብን በሚቀሰቅስበት ወቅት መካሄዱ ደግሞ ይበልጥ እንዳሳዘነዉ የገለፀዉ ማህበሩ የሚመለከተዉ አካል ጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥም ጠይቋል፡፡

ጣቢያችን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥን የጠየቅን ሲሆን መሬቱ በአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ተወስኖ በየካ ክፍለ ከተማ በኩል እንደሰጠዉ ገልፆልን የየካ ክፍለ ከተማን መጠየቅ ትችላላችሁ የሚል መልስ ሰጥቶናል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤምም የየካ ክፍለ ከተማ ስለጉዳዩ መረጃ አለዉ ፤ካለዉስ በምን አግባብ ነዉ መሬቱን ያስረከበዉ ስንል የክፍለ ከተማዉን መሬት አስተዳደር ኃላፊ ወይዘሮ ሰርካለም አስፋዉን ጠይቀናል፡፡

ኃላፊዋ እንደሚሉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ግንባታ አካሂድበታለሁ ብሎ ያሰበዉ ቦታ በሸገር ፕሮጀክት ዉስጥ የሚገኝና የታጠረ በመሆኑ ክፍለ ከተማዉ ያንን አፍርሶ ማስረከብ ባለመቻሉ ጉዳዩን ወደ አዲስ አበባ ከተማ መሬት ማኔጅመንት መልሰነዋል ብለዋል ፡፡

እኛም በጉዳዩ ላይ አዲስ አበባ ከተማ መሬት ማኔጅመንት ስራ አስኪያጅን ጨምሮ ሌሎች የቢሮ ሃላፊዎችን ለማናገር ከአንድ ሳምንት በላይ በተደጋጋሚ በእጅ ስልካቸዉ ብንደዉልም ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለዉጥን ለመዋጋት በአለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ስምምነቶችን ያደረገች አገር ስትሆን፤ በተለይም ደግሞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የአረንጓዴ አሻራን በማሳረፍ ረገድ ከፍተኛ ስራዎችን እየሰራች እንደምትገኝ ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጅ በዛዉ ልክ በብሄራዊ ፓርኮች ጭምር የሚገኙ አገር በቀል እፅዋቶች ይጨፈጫሉ ፤በሰፈራና በግብርና ምክንያትም የደን ሽፋኗ እየተመናመነ እንደሆነ የዘርፉ ተቆርቋሪዎች በተደጋጋሚ ድምፃቸዉን ያሰማሉ፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ባላደራ ማህበር የሚመለከተው የመንግስት አካል የደን ምንጣሮውን እንዲታደግ አሳስበዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
አባቱ መረቀ
ግንቦት 19 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.