ሩሲያ የበይነ-መረብ ኩባንያዎች ቢሮዋቸውን በሀገሪቱ እንዲከፍቱ የሚያስገድድ ህግ አወጣች

ከሰሞኑን የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ታላላቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን የሚገድቡ ደንብ እና ሕግጋትን ሲያወጡ ቆይተዋል፡፡

የሩሲያ ህግ አውጪዎችም የውጪ ሀገር የበይነ-መረብ ኩባንያዎች በሀገሪቱ ቢሮ እንዲከፍቱ አልያም ከባድ ቅጣትን እንዲቀበሉ የሚያደርግ ሕግ ትናንት አውጥተዋል፡፡

ሕጉ በሩስያ ውስጥ ከ500 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎች ባሏቸው ኩባንያዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ኩባንያዎቹ ይህን ህግ ተላልፈው ሲገኙ ከሚጠብቋቸው ቅጣቶች መካከል በሀገሪቱ አገልግሎታቸውን ማስተዋወቅ እንዳይችሉ፣ ክፍያንም እንዳይሰበስቡ እንዲሁም በተወሰነ መልኩ አልያም ሙሉ ለሙሉ ማገድ ይገኙበታል፡፡

ሩሲያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከታላላቅ የበይነ-መረብ ኩባንያዎች ጋር ያላት ግንኙነት ወዳጅነት የራቀው ሆኗል፡፡

ከወራት በፊት እንደ ፌስቡክ፣ ትዊተር እና ዩትዩብ ባሉት ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተሻለ ቁጥጥር የሚሰጣትን እርምጃ መውሰዷ ይታወሳል፡፡

የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቱንም ትላልቆቹ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከሀገራት ሉዓላዊነት ጋር ለመፎካከር በሚያበቃ የተፅዕንዖ ደረጀ ላይ ስለመገኘታቸው ተናግረዋል፡፡

የሀገሪቱ ቴሌኮምዩኒኬሽን ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ከአደንዛዥ እፅ፣ የህፃናት የራቁት ምስሎች እንዲሁም ታዳጊዎች እራሳቸውን እንዲያጠፉ የሚገፋፉ ትዊቶችን አላነሳም በሚል ትዊተር በሩሲያ የሚሰራበትን ፍጥነት ቀንሶታል፡፡

ትዊተር በበኩሉ በሀገሪቱ ያለው እንቅስቃሴ እንዳሳሰበው ገልጿል፡፡

ሆኖም እነዚህ እርምጃዎች በሁሉም ወገኖች ዘንድ በበጎ አልታዩም፡፡

በመጪው መስከረም ምርጫ ምታደርገው ሩሲያ እነዚህን እርምጃዎች ተጠቅማ የመንግስት አኩራፊዎችን አፍ ልትለጉም ትችላለች ሲሉ ፍራቻቸውን የሚገልፁ አሉ፡፡

የሀገሪቱ ባለስልጣናት በበኩላቸው በእስር ላይ የሚገኘው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ አሌክሲ ናቫሊን በመደገፍ የተላለፉትን የተቃውሞ ጥሪዎች ከገፃቸው ባለማጥፋት በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ እየገቡ ነው ሲሉ ክስ ያቀረቡባቸዋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ግንቦት 26 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *