ዘምዘም ባንክ በዛሬው ዕለት ስራ መጀመሩን አስታወቀ

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ከወለድ ነፃ ባንክ የሆነው ዘምዘም ባንክ በዛሬው ዕለት በይፋ ሥራ ጀምሯል ።

የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ መሊካ በድር በምረቃ ዝግጅቱ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ዘምዘም ባንክ የሼሪያን መርህ ተከትሎ በመላው የአገሪቱ ይሰራል ብለዋል።

ብሔራዊ ባንክ ለኢስላሚክ ባንክ መቋቋም መስመር ከከፈተ በኋላ ስድስት አዲስ ባንኮች ስራ የመጀመር እንቅስቃሴ ቢጀምሩም ዘምዘም ባንክ በኢትዮጵያ የኢስላሚክ ባንክን ስራ ያስጀመረ ሆኗል።

ባንኩ ወሎ ሰፈር በሚገኘው በአረበኛ የመጀመሪያ በሆነው ፊደል ” አሊፍ ” ተብሎ በተሰየመ ቅርንጫፉን ስራውን በይፋ ጀምሯል።

ባንኩ 871.9 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታልና 1.7 ቢሊዮን ጥቅል ካፒታል አንዳለው ተነግሯል።

በተለይም በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩና የፋይናንስ ተደራሽነት በሌለባቸው አካባቢዎች በስፋት እንደሚሰራ አስታውቋል ።

ባንኩ በኢትዮጵያ ካሉ ባንኮች ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ተወዳዳሪ ለመሆን እንደሚሰራም ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል ።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በበኩላቸው ፣ ዘምዘም የመጀመሪያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የሚሠጥና የፋይናንስ ተደራሽነት ለማስፋት እንደሚሠራም ተናግረዋል ።

በተለይም ባንኩ የፋይናንስ ተደራሽነትን ከማስፋት አኳያ በአገሪቱ የገጠር ክፍሎችም እንዲሰራ ጠይቀዋል ።

ባንኩ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን እና የሁሉንም የዕምነት ተከታዮች ያለምንም ልዩነት የሚያስተናግድ መሆኑም ተነስቷል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴም በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈው ፣ዘምዘም ባንክ ተወዳዳሪ ና የአገሪቱን የፋይናንስ ተደራሽነትን ከማሳደግ አኳያ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል ።

ዘምዘም ባንክ ፥ የኮር ባንኪንግ ሲስተሙ ዘመናዊ እንደሆነ ገልፆ በሲስተም አቅራቢዎችና በሸሪአ ባለሞያዎች በኩል ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንዳለው አሳውቋል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
አባቱ መረቀ
ግንቦት 26 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *