የአዲስ አበባ ከተማ የጋራ መኖሪያ ቤት ለማግኘት ተመዝግበው የሚጠብቁ ዜጎችን ጥያቄ ለመመለስ ከ30 ዓመታት በላይ ያስፈልጋል መባሉ ተሰማ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ዶክተር መስከረም ዘውዴ፣ በአዲስ አበባ ከ650 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተመዝግበው ቤት በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ አስተዳደሩ ከዚህ በፊት ይተገብረው በነበረው አሰራር ጥያቄውን ለመመለስ ከ30 ዓመታት በላይ ያስፈልጋል ብለዋል።

በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ አማራጮች እየተተገበሩ መሆናቸውን የተናገሩት ሀላፊዋ፤ ከውጭ ሀገር ቤት አልሚ ኩባንያዎች ጋር በጋራ በመስራት ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻል አንስተዋል፡፡

በዚህም ከተባበሩት አረብ ኢሚሬቶችና ከደቡብ አፍሪካ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውሰው፤ ኩባንያዎቹ በዘርፉ ያለውን የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ችግር እንደሚፈቱም ጠቁመዋል።

የቢሮ ሃላፊዋ ይህን ያሉት ሰሞኑን ከደቡብ አፍሪካው ፕሮፐርቲ 2000 ጋር የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ የሚናፈሱ መረጃዎች ለማስተባበል ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

ፕሮፐርቲ 2000 በየተሰኘው የደቡብ አፍሪካ የቤት ልማት ኩባንያው ከ31 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው መሆኑንና በኢትዮጵያ ለመሰማራት ከሶስት አመታት በላይ ፍላጎቱን ሲያሳይ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

በዳዊት አስታጥቄ
ሰኔ 01 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.