የእስክንድር ነጋ ደህንነት በማረሚያ ቤት ስጋት ፈጥሩብናል አለ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ

የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት እና እጩ የሆነው እስክንድር ነጋ በአዲስ አበባ ቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት በግፍ ታስሮ የሚገኝበት ሁኔታ ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረበት ገልጻል፡፡

ፓርቲው ትናንት አጠር ያለ መግለጫ በማህበራዊ ገጹ አስፍሯል፡፡

የእስክንድር ነጋ አያያዝ ፓርቲው ሲከታተል የቆየ ሲሆን፣ በተለይም ከግንቦት 27 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ ቀድሞ ታስሮበት ከነበረው “ዋይታ” ተብሎ ከሚጠራው ዞን በደረሰበት የሰብዓዊ በደል ምክንያት 8ኛ ዞን ተብሎ ወደሚጠራው ቦታ እንዲዛወር ተደርጓል ብሏል መግለጫው ፡፡

ሆኖም አሁን ታስሮ ባለበት ቦታ በእስረኞች የደህንነቱ ሁኔታ፣ አደጋ ላይ እንደወደቀ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ማረሚያ ቤቱ ድረስ በመሄድ ለማረጋገጥ እንደቻሉም ያነሳል ፡፡

እስክንድር ነጋ እየገጠመው ያለውን የደህንነት አደጋ፣ ማረሚያ ቤቱም ሆነ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ እያወቁ መፍትሄ ለመስጠት ባለመፈለጋቸው ባልደራስ አዝኗል፤ ችግሩ ከኦህዴድ/ብልጽግና የበላይ አካላት የተሰጠበት ፖለቲካዊ አቅጣጫ እንደሆነ የሚያሳይ ሆኖ አግኝተነዋል ነው ያለው ፓርቲው፡፡

የቃሊቲ ማረሚያ ቤትም ሆነ በሕግ የእስረኞችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት የተጣለበት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የእስክንድር ደህንነት አደጋ ላይ በመውደቁ ምክንያት ሊፈጠር ለሚችል ማናቸውም ነገር ሙሉ ለሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

የእስክንድር ነጋ ደህንነት ኦህዴድ/ብልጽግና በፍትህ አደባባይ ለደረሰበት ውርደት መበቀያ ሳይሆን የመላ ሀገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ቀይ መስመር መሆኑን ተረድቶ፣ ለተፈጠሩ ችግሮች ባስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ ፓርቲያችን መንግሥትን ማሳሰብ ይወዳል ሲል አሳውቋል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን፣ዜናዎችን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሰኔ 02 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.