ባህላዊ የዕርቅና የግጭት አፈታት ዘዴ እሴቶችን ዋጋ ዝቅ አድርገን ማየታችን ኢትዮጵያ አሁን ለገጠማት ችግር ትልቅ ድርሻ አለዉ—-የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች

በዓለም ዕርቅና ሰላም ግብረሰናይ ድርጅት አዘጋጅነት የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ግጭቶችን በሰላም እንዴት መፍታት እንችላለን በሚል ጉዳይ ላይ ምክክር እየተካሄደ ይገኛል።

በምክክር መድረኩ የተገኙትና በድርጅቱ አማካሪ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ብርሀነ እየሱስ ሱራፌል እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ የቀደምት ሃይማኖት ተቀባይና ጠባቂ፣ እንዲም የውብ ባህላዊ ባለቤት መሆኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እስካዛሬ ድረስ በሰላም የቆየችው ግጭት ሳይፈጠር ቀርቶ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያን ግጭቶቻቸውን በባህላዊና ሃይማኖታዊ ስርዓቶች ተጠቅመው መፍታት ስለቻሉ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያዊን አሁን ለገጠሙን አለመግባባቶች በየሃይማኖታችንና ባህላችን መሰረት ተወይይተን መፍታት እንችላለን፤እነዚህን እሴችንም ልናከብራቸውና ልንጠቀምባቸው ይገባል ብለዋል።

እንዲሁም ሼህ ሙሃመድ ኑር አወል ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢትዮጵያ ያኔ የእስልምና ሃይማኖት ወደ ሐበሻ ምድር መግባት ሲጀምር፣ ጥንት ኢትዮጵያዊያን በውብ እንግዳ ተቀባይነት ባህላቸው መሰረት ሃይማኖታቸውን ሳይሆን ሰው መሆናቸውን ተረድተው ከነብዩ ሙሃመድ የመጡ እንግዶችን ተቀብለው ያስተናገዱ መሆናቸውን አውስተዋል።

በመሆኑም ብንጠቀምባቸውና ብንጠብቃቸው በሀገራችን ሰላምንና መዋደድን ለማምጣት ያሉን ሃይማኖቶችና ባህላዊ እሴቶቻችን ከበቂ በላይ ናቸው ነዉ ያሉት።

አባ ገዳ ካላ ገዛሃኝ ወ/ዳዊት በበኩላቸው፣ ይቅርታ ከሌለ፣ ቂም በቀልነት ካልተተወ ሰላም እንደማይረጋገጥ ገልጸዉ፣ ሰላምን ማምጣት ካስፈለገ ቂም በቀለኝነትን መተው እና ለግጭት የሚዳርጉ ታሪኮችን ከማጉላት ይልቅ አንድና ሊያስተሳስሩን የሚችሉ እስቴችን ማጎልበት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ሀገራችን ግጭትን ለመፍታት ድንቅ ባህላዊ ዘዴዎችን የመሰረቱ፣ የመሰረቱ ብቻም ሳይሆን ተጠቅመውባቸው እስካሁን በሰላም ኖረውባቸዋል፤ አሁንም ቢሆን መፍትሄው ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርዓታችንን ብቻ በመጠቀም መፍታት መቻል ነው ብለዋል።

ነገር ግን ዛሬ ላይ ለእነዚህ እሴቶቻችን የምንሰጠው ዋጋ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ የእርቅና የግጭት ባህሎቻችን ሰላምን ለማምጣት ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው ተረድተን ልንጠቀምባቸዉና ለመጪው ትውልድም በሚገባ ልናስተላልፋቸዉ ይገባል ሲሉ በጋራ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በጅብሪል ሙሃመድ
ሰኔ 05 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.