ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተግባራዊ ትምህርትና ምርምር ላይ ትኩረት ሰጥተው የማይሰሩ ከሆነ የተቋማቱ ህልውና አደጋ ላይ እንደሚወድቅም ተገለጸ

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን በማድረግ ብቁ የሰው ሃይል ማፍራት ተልዕኳቸው ቢሆንም በንድፈ ሀሳብ ላይ ትኩረት በማድረጋቸው የኢንዱስትሪውን ዘርፍ እንደጎዳውም ተነግሯል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ከኢንዱስትሪዎች ጋር እንዴት ማስተሳሰር ይገባል በሚለው ላይ የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከባለድርሻ አካላት ውይይት እያደረገ ይገኛል።

የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ረጋሳ እንዳሉት ፣በአገሪቱ በርካታ የመንግስት ፣የግልና የቴክኒክ ተቋማት ቢገኙም አምራች ዜጋን ከማፍራት አንፃር ግን በስፋት እየሰሩ አይደለም ብለዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች ከኢንዱስትሪ ጋር ባለመተሳሰራቸው ዘርፉ እንዳያድግ ከማድረጉም በተጨማሪ የስራ አጥንቱን ችግር ከፍ አድርጎታል ብለዋል።

በሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር የተቋማት ትስስር ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ተፈራ በበኩላቸው ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በብዛት በንድፈ ሀሳብ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ማድረጋቸው አገሪቱ ከምርምርና ኢንዱስትሪ ተጠቃሚ እንዳትሆን አድርጓታል ብለዋል።

በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተግባር ትምህርቶችና በችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው እና ተማሪዎችን ከኢንዱስትሪዎች ጋር እንዲገናኙ ማድረግ እንዲሁም መምህራን ከአለም አቀፍ ተቋማት ልምድ እንዲወስዱ ማድረግ ይገባልም ተብሏል።

ለዚህ ደግሞ የአገሪቱን የትምህርት ፖሊሲ በመፈተሽ ከንድፈ ሀሳብ ባለፈ በተግባር ላይ የሚያተኩር ስርዐተ ትምህርት መፍጠር ያስፈልጋል ተብሏል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችንቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
አባቱ መረቀ
ሰኔ 08 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *