በመርከቦች የገቢ ጭነት ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በመደረጉ እቃ የያዙ ወደ 7 ሺህ የኢትዮጵያ ኮንቴይነሮች በተለያዩ የቻይና ወደቦች ላይ መከማቸታቸውን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ፣ በአሁኑ ወቅት የገቢ ጭነት ለማስገባት ከፍተኛ ጫና መኖሩን ለኢዜአ ገልጸዋል።

“በጥቂት ቀናት ውስጥ እቃዎችን ለማስገባት ለመርከብ ጭነት ይከፈል የነበረው ሂሳብ ከነበረበት 3 ሺህ ዶላር በአማካይ ወደ 9 ሺህ ዶላር ደርሷል” ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ዋናው በኮቪድ-19 ክልከላዎች ኮንቴይነሮች በየአገራቱ ገብተው በመቅረታቸው ከፍተኛ የኮንቴይነር እጥረት በማጋጠሙ እንደሆነ ገልጸዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደሚሉት 9 ሺህ 200 ዶላር ለ40 ጫማ ኮንቴይነር እንዲሁም ለ20 ጫማ ደግሞ 5 ሺህ 700 ዶላር እየተከፈለ ነው።

“ሁኔታው አጠቃላይ የድርጅቱን ደንበኞች ላልታሰበ ወጪና ኪሳራ የመዳረግ አዝማሚያ እየፈጠረ ነው” ብለዋል።

በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ወደ 60 በመቶ ጭነቷን ከ59 የተለያዩ የቻይና ወደቦች ላይ እያነሳች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በጥቅሉም ቢሆን በአመዛኙ ጭነት እየወጣ የሚገኘው ከቻይና በመሆኑና ሌሎች አገሮች ጭነት እያወጡ ባለመሆኑ ችግሩ ኢትዮጵያን ሰለባ አድርጓታል ብለዋል።

በተከሰተው የመርከብ የገቢ ጭነት የዋጋ መናር ምክንያት በዚህ ወቅት ከቻይና የተለያዩ ወደቦች መነሳት የነበረባቸው እቃ የያዙ ኮንቴይነሮች ተከማችተዋል።

በተለይም ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጋር የሚሰሩ የመርከብ ድርጅቶች እስከ 80 በመቶ የሚሆን ጭነት ያጓጉዛሉ።

ይህን ያህል ጭነት የሚያጓጉዙ የመርከብ ድርጅቶች በተፈጠረው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ሥራቸውን ለመቀጠል አልፈለጉም ነዉ ያሉት።

በዚህም ምክንያት ወደ 7 ሺህ ኮንቴይነሮች ከቻይና ወደቦች መነሳትና ጭነት ማጓጓዝ አልተቻለም ይላሉ።

ድርጅቱ በሚችለው አቅም የራሱን መርከቦች ተጠቅሞ ጭነቱን ለማንሳት ማቀዱንም አቶ ሮባ ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኮንቴይነር ግዢ ለመፈጸም መታቀዱንና መድኃኒትና የመከላከያ እቃዎችን ቀድሞ ለማንሳትም ታስቧል ነው ያሉት።

ጉዳዩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያጋጠመ መሆኑንም አስረድተዋል።

”ችግሩ ፈጥኖ ተፈታ ከተባለ እስከ ሦስት ወር ውስጥ ሊቀረፍ ይችላል፤ ይህ ካልሆነ ግን እስከ ፈረንጆቹ 2021 መጨረሻ ድረስ ሊቀጥል ይችላል” ብለዋል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችንቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ሰኔ 09 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.