በኢትዮጵያ በየአመቱ ከ 36 ሺህ በላይ ህጻናት በአየር ብክለት ምክንያት ህይወታቸውን እንደሚያጡ ተነገረ።

በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ ያለዉ የአየር ብክለት የአለም ጤና ድርጅት ካስቀመጠው ስታንደርድ ከሁለት እና ሶስት እጥፍ በላይ መሆኑ ነዉ የተገለጸው ።

የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን እንዳለው በፈረንጆቹ 2019 በተደረገ ጥናት በኢትዮጵያ በአመት ከ77 ሺህ በላይ ሰዎች ለሞት የሚዳረጉ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 2 ሺህ 700 የሚሆነው የሚከሰተው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ መሆኑ ተነግሯል።

ከዚህ ውስጥ ከ67 ሺህ በላይ የሚሆኑት በቤት ውስጥ በሚከሰት የአየር ብክለት ህይወታቸውን የሚያጡ ናቸው።

በየአመቱ ህይወታቸውን ከሚያጡ 36 ሺህ 800 ህጻናት መካከልም 63 በመቶ ወይም ከ23 ሺህ በላይ የሚሆኑት በቤት ውስጥ በሚደረግ የማብሰል ሂደት በሚፈጠር የአየር ብክለት ለሞት ይዳረጋሉ ነው የተባለው።

በዚህም ከተመጣጠነ የምግብ እጥረት ቀጥሎ የአየር ብክለት በኢትዮጵያ በርካታ ሰዎችን ለሞት በመዳረግ ሁለተኛው ነው።

ይህም ኢትዮጵያ የአየር ብክለትን ለመከላከል ችግኝ ከመትከል ያለፈ ስራ መስራት እንደሚጠበቅባት አመላካች ነው ተብሏል።

ከተሽከርካሪዎች የሚወጣው ጭስ፣ ከህንጻ እና መንገድ ግንባታዎች ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ የአቧራ ብናኞች በተለይም በአዲስ አበባ ለሚከሰት የአየር ብክለት ዋና መንስኤዎች መሆናቸው ተጠቅሷል ።

የአለም ጤና ድርጅት ጥናት እንደሚያሳየው በአለም አቀፍ ደረጃ በአየር ብክለት ምክንያት 8 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን ያጣሉ።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችንቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
በሙሉቀን አሰፋ
ሰኔ 10 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.