የአዉሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ የተናገሩት የቅኝ ገዢ ሃሳብ መሆኑን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት የፊንላንዱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአዉሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ፔካ ሃቪስቶ በቀርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዉ ከተመለሱ በኋላ ለአዉሮፓ ህብረት ያቀረቡት ሃሳብ የጣልቃ ገብነትን አዝማሚያ የሚያሳይና ተቀባይነት የሌለዉ ሲል አጣጥሎታል፡፡

የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዉ እንደነበር ያስታወሰዉ መግለጫዉ፤ በዚህም ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ጋር ጭምር ዉይይት እንዳደረጉ ያስታወቀዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፤ይህም የኢትዮጵያ መንግስት ካለዉ ግልፀኝነት ለአዉሮፓ ብረት ካለዉ አክብሮት ነዉ ብሏል፡፡

ይሁን እንጅ የፊንላዱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአዉሮፓ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ፔካ ሃቪስቶ፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀዉ ከህወሓት ጋር መነጋገር ይገባል፤ እንዲሁም መንግስት ከህወሓት ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረግ አለበት ሲሉ ለህብረቱ ወንጅለዋል፡፡

እንዲሁም ስለ ስድስተኛዉ አገራዊ ምርጫና በትግራይ ክልል ግብርናን ለማስጀመር መንግስት እያደረገ ያለዉን ጥረት ወደ ጎን በመተዉ የኢትዮጵያ መንግስት ትግራይን ሊያጠፋ ነዉ ብለዉ ፔካ ሃቪስቶ መናገራቸዉ አሳዛኝ ነዉ ብሏል መግለጫዉ፡፡

የልዩ መልእክተኛዉ ሃሳብ ሃላፊነት የጎደለዉና፤ ከዲፕሎማሲ መርህ የወጣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ህዝብ በማሰብ ሳይሆን የቅኝ ገዢን መንፈስ የተላበሰ ሲልም የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኮንኖታል፡፡

በመጨረሻም ህብረቱ መግለጫዉን በድጋሚ እንዲያጤነዉ በመጠየቅ የኢትዮጵያ መንግስት ከአዉሮፓ ህብረት ጋር ያለዉን ግንኙነት ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን አንስቷል፡፡

በአባቱ መረቀ

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *