የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የልማት እንጅ የፀጥታ ጉዳይ ባለመሆኑ ሱዳን ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መውሰዷ ተቀባይነት የለውም ሲል የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ሱዳን እና ግብፅ የህዳሴውን ግድብ ድርድር ወደ ፀጥታው ምክርቤት እንውሰደው ማለታቸው የህብረቱን ጥረት ለማደናቀፍ በማሰብ ስለሆነ ፣ኢትዮጵያ የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ እጁን ያስገባ የሚለውን የሱዳንና የግብፅን አቋም ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው ገልጻለች ።

ግብፅና ሱዳን በአፍሪካ ህብረት የተጀመረውን ድርድር ከ9 ጊዜ በላይ አቋርጠው አሁን ደግሞ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት እንሂድ ማለታቸው ህብረቱን ብቻ ሳይሆን የሶስቱን አገራት ቀጣይ ግንኙነት እንሚሸረሽረውም የውጭ ጉዳይ በመግለጫው አንስቷል።

ከዚህ በተጨማሪም ጉዳዩ የአፍሪካውያን ሆኖ ሳለ ግብፅና ሱዳን ግን ወደ ማይመለከተው የአረብ ሊግ በመውሰድ እያወሳሰቡትና አሁንም ድረስ የቅኝ ዘመን ሀሳብን እያንፀባርቁ እንደሆነም አመልክተዋል ።

ኢትዮጵያ የሶስትዮሽ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥል ፅኑ እምነት አላት ያለው መግለጫው፣ በዚህም የፀጥታው ምክርቤት ሱዳንና ግብፅ ወደ ህብረቱ ውይይት እንዲመለሱ እንዲያበራታታም ጠይቋል።

ሱዳን ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መውሰዷን ተከትሎ አስተያየት የሰጡት የሚንስቴሩ ቃልአቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ግድቡ የልማት እንጅ የፀጥታ ጉዳይ ባለመሆኑ ምክር ቤቱ ጋር መውሰድ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

ይልቁንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት ሱዳንና ግብፅ የአፍሪካ ህብረትን ድርድር እንዲያከብሩ ግፊት ያድርግ ስትል ኢትዮጵያ ጠይቃለች።

በአባቱ መረቀ
ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *