በኢትዮ ሱዳን ድንበር ላይ ያለዉ የፀጥታ ሁኔታ አስቸጋሪ በመሆኑ አርሶ አደሮች የእርሻ ስራቸዉን ለማከናወን ተቸግረዋል ተባለ፡፡

የምዕራብ ጎንደር ዞን ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳስታወቀዉ፣ በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢዎች የሱዳን ጦር በመስፈሩ የግብርና ስራን ለማከናወን አርሶ አደሮች ተቸግረዋል ብሏል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰዉ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ፤ ምንም እንኳን ወቅቱ የእርሻ ወቅት ቢሆንም በአካባቢዉ ባለዉ የፀጥታ ችግር ምክንያት አርሶ አደሮች የግብርና ሥራቸዉን ለማከናወን መቸገራቸዉን ተናግረዋል፡፡

የሱዳን ጦር ከሁመራ ድንበር እስከ ቋራ ባለዉና እስከ 5 መቶ ኪሎሜትር በሚያካልለዉ ስፍራ ላይ በመስፈሩ ለአካባቢዉ አርሶ አደሮች የፀጥታ ሁኔታዉ አስቸጋሪ ሆኗል ነዉ ያሉት፡፡

የምዕራብ ጎንደር ዞን ባለዉ አደረጃጀት ፀጥታዉን ለማስከበርና ለአርሶ አደሮች ድጋፍ ለማድረግ እየሞከረ ቢገኝም ችግሩ ከዞኑ አቅም በላይ እንደሆነም አቶ ደሳለኝ ተናግረዋል፡፡

ወቅቱ ሰብል የሚዘራበት በመሆኑ የክልሉና የፌደራል መንግስት ለአርሶ አደሮቹ አስፈላጊዉን ጥበቃ አድርገዉ ወደ ግብርና ስራቸዉ እንዲመለሱም ዋና አስተዳዳሪዉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ ባለፈዉ አመት ያረሱትን ሰብል ሳይሰበስቡ፣ በሱዳን ጦር መፈናቀላቸዉ የሚታወስ ሲሆን ፤በያዝነዉ የመኸር እርሻ እነዚህ አርሶ አደሮች የማያርሱ ከሆነ የሰዉ እጅ ተጠባባቂ እንደሚሆኑም አቶ ደሳለኝ አንስተዋል፡፡የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ከተቆጣጠረ ጀምሮ በየቀኑ የተለያዩ ትንኮሳዎችንና ጥቃቶችን እንደሚፈፅምም ታዉቋል፡፡

ከዚህ ቀደም የችግሩ ሰለባ የሆኑት አርሶ አደሮች ቁጥር 450 እንደነበሩ የሚናገሩት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ፤ አሁን ላይ የሱዳን ጦር በየቀኑ የተለያዩ ትንኮሳዎችን ስለሚያደርግ በርካቶች እየተፈናቀሉ ነዉ ተብሏል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

በአባቱ መረቀ

ሰኔ 23 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *