“የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ሰኔ 21/2021 ዓ.ም. የወሰደው ‘በሰብዓዊ ምክንያት ተኩስ የማቆም አዋጅ’ ትግራይ ውስጥ ላለውን ግጭት መፍትኄ ለማግኘት ትክክለኛ እርምጃ በመሆኑ እንደግፈዋለን” ሲሉ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ትግራይ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲገኝ መንገድ ለመጥረግ እንዲቻልም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አጠቃላይና ሁሉን አቀፍ የሆነ ቋሚ ተኩስ ማቆም ላይ እንዲደረስ እንዲሠሩ የኅብረቱ ሊቀ መንበር ጠይቀዋል።
ለዚህም ሁሉም ዓይነት የግጭት ሁኔታዎች እንዲቆሙ ፤ በዓለም አቀፍ ህግ መሠረት ሲቪሎችን ከአደጋ ለመጠበቅ እና ክልሉ ውስጥ ለተጎዱት ሁሉ እጅግ አስፈላጊ አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ የሰብዓዊ እርዳታ ተዋናዮች ደኅንነቱ የተረጋገጠ ተደራሽነት እንዲኖራቸው ለማስቻል ሁሉም ወገኖች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አድርገዋል።
ለትግራይ ክልል ግጭት የፖለቲካ መፍትኄ እንዲፈለግም ሊቀ መንበሩ በተጨማሪ መጠየቃቸውንና በሃገሪቱ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ጥረቶች የአፍሪካ ኅብረት ድጋፉን ለመስጠት ያለውን ያልተቋረጠ ዝግጁነት ማሳወቃቸውን ከፅ/ ቤታቸው የወጣው መግለጫ ይጠቁማል።
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያውያን
ሰኔ 23 ቀን 2013 ዓ.ም











