በአሁኑ ወቅት በሚሊኒየም የቮቪድ 19 ማገገሚያ ማእከል ህክምና እየተደረገላቸዉ የሚገኙ ታካሚዎች 21 ብቻ ናቸዉ ተባለ፡፡

ወደ ሚሊኒየም የኮቪድ19 ማገገምያ ማእከል የሚገቡ ዜጎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ተነግሯል፡፡

በአሁኑ ሰአት በማገገሚያ ማእከሉ ውስጥ የሚገኙ ታካሚዎች ቁጥር 21 ብቻ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 17 ያህሉ አጋዥ የመተንፈሻ መሳርያ የተገጠመላቸው ናቸው ተብሏል፡፡

የሚሊኒየም ኮቪድ 19 ማገገምያ ማእከል ክሊኒካል ዳሬክተር ዶ/ር አቤል ሙራጃ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት፣ ወደ ማእከሉ የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥር እየቀነሰ ይገኛል ብለዋል፡፡

አሁን ላይ በማእከሉ ከሚገኙ ታካሚዎች ውስጥ አራት ታካሚዎች ሙሉ በሙሉ አገግመው ወደ ቤተሰቦቻቸው ሊቀላቀሉ እንደሆነም ነግረውናል፡፡

ባለፈው 2012 አመት ልክ በዚህ ሰአት በማእከሉ የነበሩ ታካሚዎች ቁጥር ከ800 በላይ እንደነበረ ያስታወሱት ዶ/ር አቤል፣ በዚህ ሰአት ግን የታካሚዎች ቁጥር እጅጉን ቀንሷል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በያዝነው መጋቢት ወር ላይ እንኳ የታካሚዎች እና የመተንፈሻ መሳርያ የሚፈልጉ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ እንደነበረ ገልጸዉ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ያንን አይገልጽም ነው ያሉት፡፡

ታካሚዎቹን የሚንከባከቡ የጤና ባለሙያዎች አሁንም በማእከሉ እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን አሁንም መዘናጋት እንደማያስፈልግ ባለሙያዉ አሳስበዋል፡፡

በሀገሪቷ እስካሁን ድረስ ከ276ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ ከነዚህ ውስጥ ከ260ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ማገገማቸው ነው የተገለጸው፡፡

እንዲሁም 4ሺህ 320 ዜጎች ደግሞ በቫይረሱ አማካኝነት ህይወታቸው ማለፉም ተነግሯል፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

በሔኖክ ወ/ገብርኤል

ሰኔ 24 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *