የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር የተቀማሁትን መስሪያ ቤት ይመለስልኝ ሲል መንግስትን ጠየቀ

በምህፃረ ቃሉ ወ.ወ ክ.ማ ተብሎ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር አራት ኪሎ የሚገኘው የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን የሚጠቀምበት ህንፃ መንግስት ይመለስልኝ ሲል ጠይቋል ።

መስሪያ ቤቱ በደርግ መንግስት እንደተቀማ የሚገልፀው ማህበሩ፣ለበርካታ አመታት የይመለስልኝ ጥያቄ ብጠይቅም መንግስት ጥያቄያችንን እንዲመልስልን ሲሉ የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ኢትዮጵያ ጥላሁን ጠይቀዋል ።

በአሁኑ ሰዐት በህንፃው ቅጥር ግቢ ውስጥ የአዲስ አበባ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን የጀመረውን የህንፃ ግንባታ እንዲያቆም ሲል ማህበሩ አሳስቧል።

ከዚህ ቀደም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ህንፃው እንደሚመለስልን ቃል የተገባ ቢሆንም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ህልፈት ተከትሎ እስካሁን ድረስ ምላሽ አለማግኘቱም ነው የተገለጸው ።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ህልፈት በኋላ ባሉት አመታትም ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ፣ ለቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንዲሁ ለወይዘሮ አዳነች አበቤ አስተዳደርም ጥያቄውን በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ምላሽ ግን አላገኘንም ብለዋል።

ይባስ ብሎ አሁን ላይ በቀድሞው የማህበሩ ግቢ ውስጥ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ህንፃ ለማስገንባት ቁፋሮ መጀመሩ እንዳሳዘነው አስታውቋል።

በዚህም መንግስት ግንባታውን አስቁሞ ህንፃውን እንዲያስመልስልን ሲል ጠይቋል ።

የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት በ1942 ዓ.ም የተመሠረተ ሲሆን ለአገሪቱ ስፖርት፣ጥበብና በሌሎችም ዘርፎች ትልቅ አስተዋጽኦ ስለማድረጉም ተነግሯል ።

ወ.ወ.ክ.ማ፣በማህበራዊ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢኮኖሚ ፣በስፖርት፣ በበጎፍቃደኝነት፣ በህይወት ክህሎት እና አመራር ብቃት ላይ በስፋት የሚሰራ ማህበር ነው።

በአሁኑ ወቅት ከ30ሺህ በላይ አባላት ያሉት ሲሆን በየአመቱም ከ80ሺህ በላይ ዜጎችን የፕሮጀክት ተጠቃሚ ማድረጉንም አስታውቋል።

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

በአባቱ መረቀ

ሐምሌ 01 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published.