በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተነሳውን ውዝግብ ለመፍታት የአፍሪካ ህብረት በጣም ተገቢው ስፍራ እንደሆነም እናምናለን ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ተናገሩ ፡፡

የናይል ውሃን እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል ማወቅ ለሶስቱም ሀገሮች አስፈላጊ እንደሆነ እንረዳለን እናም በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ፍትሃዊ መፍትሄ ለማግኘት ከሁሉም ወገኖች የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ሲሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ተናገሩ፡፡

በትላንትናው እለት በጸጥታው ምክር ቤት ንግግር ያደረጉት አምባሳደር ሊንዳ ቶምሰን-ግሪንፊልድ እንዳሉት ድርድሩ ውጤታማ የሚሆነው ፣ ተጨባጭ ድርድሮችን እንደገና በመጀመር ነው ብለዋል ፡፡

እነዚህ ድርድሮች በአፍሪቃ ህብረት መሪነት በአስቸኳይ መምከር አለባቸው ብለዋል፡፡

ሂደቱም በሶስቱም ወገኖች የተፈረመውን የ 2015 መርሆዎች መግለጫ እና በሀምሌ 2020 በአፍሪካ ህብረት የተሰጠውን መግለጫ እንደ መሰረታዊ ማጣቀሻዎች መጠቀም ይኖርበታል በማለት ገልጸዋል ፡፡

ይህንን ውዝግብ ለመፍታት የአፍሪካ ህብረት ተገቢው ስፍራ ነው ያሉት አምባሳደሯ፤ አሜሪካ የተሳካ ውጤት እንዲመጣ ለማመቻቸት የፖለቲካ እና የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠት ቁርጠኛ ናት ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት እና የሶስቱ ኦፊሴላዊ ታዛቢዎች – ደቡብ አፍሪቃ ፣ የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት እና ሌሎች አጋሮች አዎንታዊ ውጤትን ለማስገኘት ያላቸውን እውቀትና ድጋፍ እንዲጠቀሙ እናሳስባለን ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም የሱዳን ፣ የኢትዮጵያ እና የግብፅ ተወካዮች ውጥረቱን ለማብረድ የሚቻላቸውን መንገዶች በሙሉ ከመንግስታችን ጋር መወያየታቸውን እንዲቀጥሉ እና ይህን ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ እንዲሆኑ ጥሪ አስተላልፈዋል ፡፡

ሁሉም ወገኖች ማንኛውንም መግለጫ ከመስጠት ወይም የድርድር ሂደቱን አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ እርምጃዎች እንዲቆጠቡ እና በሁሉም ተደራዳሪዎች ዘንድ ተቀባይነት ወዳለው የድርድር መፍትሄ እንዲመጡ ጠይቀዋል ፡፡

በግድቡ ላይ መፍትሄ መድረስ በውሃ ሀብቶች ፣ በቀጠናዊ ልማት እና በኢኮኖሚ ውህደት ላይ ተጨማሪ ትብብር ለማድረግ መንገድ ይከፍታል ነው ያሉት፡፡

በአፍሪካ ህብረት የሚመራው ድርድር በአስቸኳይ እንዲጀመር እና ወደ ፍሬያማ ፣ ተጨባጭ እና ገንቢ ፍፃሜዎች እንዲሸጋገር ከግብፅ ፣ ከኢትዮጵያ እና ከሱዳን እንዲሁም ከአጋሮቻችን ጋር ለመስራት አሜሪካ ቁርጠኛ አቋም አላት ብለዋል አምባሳደሯ ፡፡

ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።

ያይኔአበባ ሻምበል

ሐምሌ 02 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *