በቀድሞ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ምክንያት በተነሳው አመፅ የሟቾች ቁጥር 30 ደረሰ

ባለፈው ሳምንት ሀሙስ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ እጃቸውን ለፖሊስ መስጠታቸውን ተከትሎ አንዳንድ የደቡብ አፍሪካ አካባቢዎች በተቃውሞ ተጥለቅልቀዋል

ከእርፍት ቀናቱ ወዲህ ግን ተቃውሞዎቹ እየባሱ ሄደው ወደ ከፍተኛ አመፅነት ተቀይረዋል፡፡

እሳቶች እየተቀጣጠሉ ነው፣ ንግድ ቤቶች እየተዘረፉ ነው፣ መንገዶች እየተዘጉ ነው፡፡

ጦር ሀይሉ ረብሻው ከአቅሙ በላይ የሆነበትን ፖሊስ ለመርዳት አመፅ ባለባቸው ቦታዎች ላይ ተሰማርቷል፡፡

የፖሊስ ሚኒስትሩ ቤኪ ሴል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ዘረፋው የሚቀጥል ከሆነ በመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችና ቁሳቁሶች ዕጥረት ምክንያት አደጋ ውስጥ የሚወድቁ በርካታ አካባቢዎች ይኖራሉ ብለዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትሩ ኖሲቪዌ ማፒሳ ንካኩላ ግን ለዚች አመፅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ አያስፈልግም ፤እንቆጣጠረዋለን እያሉ ነው፡፡

የዙማን መታሰር እንደ ጥሩ አጋጣሚ የቆጠሩ ወንጀለኞችና የወንበዴ ቡድን ናቸው ይሄን ትርምስ የፈጠሩት እያሉ ነው የመንግስት ባለስልጣናት፤ ሌሎች ደግሞ ስራ አጥነትና ድህነት ተቃውሞውን እንዳቀጣጠሉት እየገለፁ ነው፡፡

የፖሊስ ሚኒስትሩ ቤኪ ሴል የቱንም ያህል በመንግስት አለመደሰታችን፣ ወይም የግል ኑሮና ሁኔታችን አሳዛኝ መሆን፤ የፈቀደንን እንድናደርግ፣ እንድንዘርፍ፣ እንድናወድም፣ ህግ እንድንተላለፍ መብት አይሰጠንም ሲሉ በማስጠንቀቂያ መልክ ገልጸዋል፡፡

ጃኮብ ዙማ በሳቸው የስልጣን ዘመን ለተሰራ የሙስና ወንጀል ፤ ፍርድ ቤት ተገኝተው መረጃ ባለመስጠታቸውና በምርመራ ሂደቱ ባለመሳተፋቸው ፤ ለፍርድ ቤት ባለመታዘዝ በሚል የተፈረደባቸው ባለፈው ወር ነበር፡፡

የ 79 አመት ዕድሜው ዙማ ሙስናውን አላውቅም ሲሉ ቢክዱም፤ ባለፈው ሳምንት ለፖሊስ እጃቸውን ሰጥተዋል፡፡

የ 15 ወር እስራት የተፈረደባቸው ቢሆንም ዙማ ግን በሀገሪቱ የህገ መንግስት ፍርድ ቤት ፍርዳቸው በድጋሚ እንዲታይላቸው ወይ የፍርድ መጠኑ እንዲቀንስላቸው ተስፋ አድርገዋል፡፡

የህግ ባለሙያዎች ግን ዕድላቸው ጠባብ እንደሆነ እየገለፁ ነው፡፡

በዚህ ምክንያት በተቀሰቀሰው አመፅ የ 15 አመት ታዳጊን ጨምሮ ቢያንስ 30 ሰዎች ህይወታቸው እዳለፈ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በሔኖክ አስራት
ሐምሌ 06 ቀን 2013 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *