የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እንዳስታወቀዉ ወቅቱ ክርምት በመሆኑ ሊከሰት የሚችለዉን አደጋ ለመከላከል ከክልሎች ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝና የአፋር ክልልም 4 ጀልባዎች ለመግዛት በሂደት ላይ ነዉ ብሏል፡፡
የኮሚሽኑ የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘዉዴ ከኢትዩ ኤፍ ኤም ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ለጎርፍ አደጋ እና ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ በሆኑ የአገሪቱ አካባቢዎች የቅድመ መከላከል ስራዎች እየተሰራ እንደሚገኝ አስታዉቀዋል፡፡
ሁሉም ክልሎች እና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸዉን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ አማራ ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች ደግሞ ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ ናቸዉ ተብሏል፡፡
በዚህ አመት የባለፉት አመታት አይነት አደጋዎች እንዳይከሰቱ ከክልሎች ጋር በጋራ በመሆን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሆነም አቶ ደበበ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ባለፈዉ አመት የጎርፍ አደጋን አስተናግዶ የነበረዉ የአፋር ክልል በዚህ አመት አደጋን ለመከላከል 45 ሚሊዮን ብር ክልሉ መድቦ ወደ ስራ መግባቱም ታዉቋል፡፡
በክልሉ ሊከሰት የሚችለዉን የጎርፍ አደጋ ግምት ዉስጥ ማስገባት 4 ጀልባዎችን ለመግዛት የግዥ ሂዳት ላይ እንደሚገኝም ነዉ ዳይሬክተሩ የገለፁት፡፡
የሶማሌ እና የአማራ እንዲሁም ሌሎች ተጋላጭ የሆኑ ክልሎችም ግድቦችን ጭምር በመገንባት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን እንደሰሩ ተነስቷል፡፡
ከዚህ ባለፈ ግን አደጋዎቹ ቢከሰቱ ለተጎጂዎች የተለያዩ እርዳታዎችን በፍጥነት ለማድረስ ያስችል ዘንድ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን መንገዶችን በመጠገን አስፈላጊዉን ድጋፍ እንዲያደርግም ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል፡፡
የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ ተጎጂዎች አስፈላጊዉን እርዳታ ማድረግ የሚስችል አቋም ላይ እንደሚገኝም ሰምተናል፡፡
ውድ አድማጮቻችን እና ተከታዮቻችን የኢትዮ ኤፍ ኤም ስርጭቶችን ቻናላችንን እና ሌሎች ዝግጅቶችን ለመከታተል የቴሌግራም ቻናላችንን https://t.me/ethiofm107dot8 ይቀላቀሉ።
አባቱ መረቀ
ሐምሌ 08 ቀን 2013 ዓ.ም











